“ግብርና ግን ለአማራ ሕዝብ ከፖለቲካም ከልዩነትም በላይ ነው” ድረስ ሳኅሉ (ዶ.ር)

57

ባሕር ዳር: የካቲት 27/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ባለፈው ዓመት የምርት ዘመን በክልሉ በተለያዩ ችግሮች ምክንያት በበቂ መጠን ያልደረሰው የግብርና ግብዓት በክልሉ ምርት እና ምርታማነት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሮ አልፏል፡፡ በክልሉ የተስተዋለው የምርት እና ምርታማነት መቀነስ ከክልሉ አልፎ ሀገራዊ ውስንነቶችንም ፈጥሯል።

ክልሉ በተያዘው የምርት ዘመን 165 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ቢያቅድም የቁም ሰብል ግምገማው ውጤት ግን ከ145 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰብ እንደማይቻል አመላክቷል፡፡ በክልሉ የተፈጠረው ሰው ሰራሽ እና የተፈጥሮ ችግሮች በክልሉ ምርት እና ምርታማነት ላይ የጎላ ክፍተት ፈጥረዋል ነው የተባለው፡፡

በተለይም በክልሉ በርካታ አካባቢዎች ላይ ካለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ጀምሮ የተፈጠረው የፀጥታ መደፍረስ ችግር በግብርና ሥራዎች ላይ ውስንነት መፍጠሩን በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ልማት ዘርፍ አሥተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳኅሉ (ዶ.ር) በተለይም ለአሚኮ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡

የፌደራል እና የክልሉ መንግሥት የግብርና ቤተሰቦች ባለፈው ዓመት ከምርት እና ምርታማነት ተፅዕኖ ባሻገር የመልካም አሥተዳደር ችግር የነበረው የግብዓት አቅርቦት ውስንነት ዳግም እንዳይፈጠር ከምንጊዜውም በተሻለ የአፈር ማዳበሪያ ግዥ ቀድሞ መፈጸሙን የቢሮ ኀላፊው ጠቁመዋል፡፡ ከጥቅምት ወር መጨረሻ ጀምሮ የአፈር ማዳበሪያ ከወደብ ወደ ክዘና ማዕከላት የማጓጓዝ ሥራዎች ተጀምሮ እንደነበርም ጠቁመዋል፡፡

ነገር ግን በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች የተፈጠረው የፀጥታ መደፍረስ ችግር በግብርና ሥራዎቻችን በተለይም በግብዓት ማቅረብ ላይ ውስንነት ፈጥሯል ብለዋል ዶክተር ድረስ በመግለጫቸው፡፡ ለአማራ ክልል 8 ሚሊየን 57 ሺህ 900 ኩንታል ማዳበሪያ ግዥ ተፈጽሞ ወደ ወደብ እየተጓጓዘ ቢኾንም እስካሁን ድረስ ለአርሶ አደሩ የደረሰው ግን ከ459 ሺህ 175 ኩንታል የማይበልጥ ነው ብለዋል፡፡

የአፈር ማዳበሪያን ከወደብ ወደ ክዘና ማዕከላት ለማጓጓዝ የሚፈጀው ከስድስት ቀናት ባይበልጥም በተፈጠረው ችግር ከ30 እስከ 34 ቀናት ተሸከርካሪዎች እንዲቆሙ እየተገደዱ መኾኑን ገልጸዋል። የግብዓት ዝርፊያ፣ የተዛባ መረጃ ሥርጭት እና ባለሙያዎች በሚፈልጉት መልኩ ተንቀሳቅሰው እንዳይደግፉ መደረጉ የከረመውን የአርሶ አደሮችን ችግር የሚያባብስ ካልኾነ በቀር የሚለውጠው ነገር አይኖርም ብለዋል፡፡

በክልሉ ልዩነቶችም ኾኑ የፖለቲካ ቅሬታዎች ይኖራሉ ያሉት ዶክተር ድረስ “ግብርና ግን ለአማራ ሕዝብ ከፖለቲካም ከልዩነትም በላይ ነው” ብለዋል፡፡ የአርሶ አደሮችን የግብዓት አቅርቦት ማስተጓጎል እና ምርታማነትን መፈታተን ለአማራ ሕዝብ እጨነቃለሁ ከሚል የሚጠበቅ አይደለም ነው ያሉት፡፡

ሕዝቡም ባለፈው ዓመት የምርት ዘመን የግብዓት አቅርቦት ውስንነት ሲፈጠር ቅሬታ እና ተግሳጹን እንደገለጸው ሁሉ አሁንም የማዳበሪያ ሥርጭት በአግባቡ እንዳይከናወን የሚያውኩ ቡድኖችን ሊታገላቸው እና “ይበቃል” ሊላቸው ይገባል ብለዋል፡፡

የፌደራል እና የክልሉ መንግሥት የፀጥታ ኃይሎችም ለአርሶ አደሮች የማዳበሪያ አቅርቦት እንዲደርስ የሚያደርጉትን ድጋፍ የክልሉ መንግሥት ያመሰግናል ያሉት ዶክተር ድረስ በቀጣይ ጊዜያት በሚኖረው ሥርጭት አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡ አስፈላጊ ከኾነም የተለየ ስምሪት እና ትኩረት በመስጠት ሥርጭቱ የተሳካ እንዲኾን የበኩላቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleሕዝቡ ከመንግሥት የፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ሰላሙን እና መሠረተ ልማቶቹን እንዲጠብቅ የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አሳሰበ።
Next articleበወቅታዊ ችግር ምክንያት ክፍተት እየታየበት ያለውን ትምህርት ለማስቀጠል የድጋፍ ጥሪ ቀረበ።