
ባሕር ዳር: የካቲት 27/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ሕዝቡ ከመንግሥት የፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ሰላሙን እና መሠረተ ልማቶቹን እንዲጠብቅ የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አሳስቧል። የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር እንየው ዘውዴ በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የተከሰተውን የኤሌክትሪክ ተሸካሚ መሥመሮች መቋረጥን አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል።
ምክትል ኮሚሽነር እንየው በአማራ ክልል የተለያዩ ቦታዎች በደቡብ ጎንደር ዞን ነፋስ መውጫ አካባቢ እና በምሥራቅ ጎጃም ዞን ደብረወርቅ አካባቢ የኤሌክትሪክ ኃይል ተሸካሚ መሥመሮች ስለተመቱ በክልሉ ሰፊ አካባቢዎች የኃይል መቋረጥ መከሰቱን ገልጸዋል።
ማኅበረሰቡ የሚፈጠሩ ችግሮችን እና የችግሮችን ምንጭ በትክክል መገንዘብ እንደሚገባው አመላክተዋል። ምክትል ኮሚሽነሩ ”የኃይል መቋረጥ ችግሩን የፈጠሩት የሕዝብን ጥያቄ እናስመልሳለን በማለት ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ አካላት ናቸው፤ መብራት አጥፍቶ ሌላውን የኅብረተሰብ ክፍል ችግር ውስጥ ለመክተት አልመው የፈጠሩት የጭካኔ ተግባር ነው” ሲሉም ገልጸዋል። መብራት ሲጠፋ የውኃ አገልግሎት፣ ወፍጮ ቤቶች እና ሌሎች ማኅበራዊ አገልግሎቶች እንደሚቋረጡ ያነሱት ምክትል ኮሚሽነሩ በዚህም የሚሰቃየው የአማራ ክልል ሕዝብ መኾኑን ገልጸዋል።
ምክትል ኮሚሽነር እንየው ከዚህ በፊትም የትራንስፖርት አግልግሎት የሚሰጥባቸው መንገዶች እና ድልድዮች መቆረጣቸውን እና ለአርሶ አደሩ የሚጓጓዝ ማዳበሪያ ለተገልጋዩ እንዳይደርስ እክል ሲፈጠር መቆየቱን ገልጸዋል። ይህ ችግር ከጊዜ ወደ ጊዜ የክልሉን ደኅንነት እና የማኅበረሰቡን ሕልውና የሚፈታተን እና አደጋ ላይ የሚጥል መኾኑን መረዳት ይገባልም ብለዋል። ስለኾነም ሕዝቡ ከክልሉ የፀጥታ መዋቅር ጎን በመኾን በመሰረተ ልማቶች ላይ ጉዳት የሚያደርሱ አካላትን ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ማድረግ፣ ሰላምንም ማስፈን እንደሚገባ አሳስበዋል።
የተመቱት የመብራት ኃይል መሥመሮችን ለመሥራት መንግሥት እና የሚመለከታቸው አካላት ርብርብ እያደረጉ ነው፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ መዝራት ይመለሳል ብለዋል ምክትል ኮሚሽነሩ። በቀጣይም እንዲህ ዓይነት ችግር እንዳይፈጠር ማኅበረሰቡ ከመንግሥት ጎን በመኾን መሠረተ ልማቶችን መጠበቅ እንዳለበትም ተናግረዋል።
የክልሉ ፖሊስ ሰፊ ውይይት እና ግምገማ በማድረግ እና ከፌዴራል የፀጥታ መዋቅሮች ጋር በመቀናጀት የሕዝቡን ሰላም ለመጠበቅ እየሠራ መኾኑን ረዳት ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!