
ባሕርዳር: የካቲት 27/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት አስተባባሪ አያና ዘውዴ(ዶ.ር) በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ቅንጅታዊ አሠራር በተደረገው የተጠናከረ ክትትል እና ድጋፍ መሠረት የተገኙ ውጤቶች በርካታ መኾናቸውን ገልጸዋል።
ባለፉት ሰባት ወራት የአምራች ኢንዱስትሪዎች ወጪ ምርት መጠን እና ገቢን ለመጨመር በተደረገው ጥረትም 74 ሺህ 955 ቶን ምርት ወደ ውጪ እንዲላክ ክትትልና ድጋፍ በማድረግ 140 ሚሊዮን 313 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ገቢ ማስገኘት ተችሏል ሲሉ ገልጸዋል።
ለከፍተኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች የብድር አቅርቦትን ለማሳደግ በተደረገው የተቀናጀ ክትትልና ድጋፍ 23 ቢሊዮን 71 ሚሊዮን ብር ብድር ማቅረብ ተችሏልም ብለዋል።
ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ሦስት ቢሊዮን 44 ሚሊዮን ብር የፋይናስ አቅርቦትን ማሳደግ እንደተቻለም ጠቁመዋል። ከዚህ ውስጥ የሊዝ ፋይናንስ ሁለት ቢሊዮን 52 ሚሊዮን ብር እንዲሁም የሥራ ማስኬጃ አንድ ቢሊዮን 384 ሚሊዮን ብር ብድር ማቅረብ መቻሉን አብራርተዋል።
ዶክተር አያና በሰባት ወር ውስጥ 129 የውጪ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት እና 292 የሀገር ውስጥ ከፍተኛ ኢንቨስትመንቶችን በመሳብ አንድ ሺህ 493 አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች እንዲቋቋሙ መደረጉን ገልጸው፤ በተለያዩ ምክንያቶች ተዘግተውና ማምረት አቁመው ከነበሩ 460 ኢንዱስትሪዎች ውስጥ 390 ኢንዱስትሪዎች ዳግም ወደ ሥራ እንዲገቡ ተደርጓል ብለዋል።
በተጨማሪም በትግራይ ክልል ብቻ 217 ኢንዱስተሪዎች ወደ ማምረት እንዲገቡ አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል ተደርጓል። በዚህም ለ120 ሺህ 667 ዜጎች ቋሚ ሥራ እድል መፍጠር ተችሏል ሲሉ ገልጸዋል።
በንቅናቄው በተከናወኑ ተግባራት እና በመደበኛ ሥራዎች አማካይነት የአምራች ኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም ከፍ ማለቱን የኢትዮጵያ ፕረስ ድርጅት ዘግቧል። በ2015 በጀት ዓመት መጨረሻ ከነበረበት 55 ነጥብ 8 በመቶ ወደ 56 ነጥብ 4 በመቶ ማሳደግ መቻሉን አንስተዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!