
ባሕር ዳር: የካቲት 27/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት አፈፃፀም 95 በመቶ መድረሱን የሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ገልጿል። ከዚህም ውስጥ የሲቪል ሥራው 98 በመቶ እንዲሁም የኤሌክትሮሜካኒካል ሥራው 78 በመቶ መድረሱ ተገልጿል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መሠረት ድንጋይ የተጣለበት 13ኛ ዓመት “በኅብረት ችለናል!” በሚል መሪ ሃሳብ ይከበራል።
የሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ፍቅርተ ታምር በሰጡት መግለጫ፤ የግድቡ አጠቃላይ አፈፃፀም 95 በመቶ ደርሷል።
የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሕዳሴ ግድብ ላይ መግባባት የተደረሰበት የከፍታችን ምልክት ነው ብለዋል።
የመሠረት ድንጋይ የተጣለበትን 13ኛ ዓመት በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚከበር ገልጸዋል። ባለፉት 13 ዓመታት 18 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር ከሕዝብ ተሳትፎ ተሰብስቧል ብለዋል።
የመንግሥት ቁርጠኛ አቋምና የዲፕሎማሲ ጥረት እንዲሁም የመላው ኢትዮጵያውያን ድጋፍ ውጤት መሆኑን ገልጸዋል። የይቻላል መንፈስ የፈነጠቀ ታላቅ ፕሮጀክት መሆኑን ገልጸው፤ በቀጣይም መሰል ፕሮጀክቶችን በተባበረ ክንድ መፈፀም ይገባናል ብለዋል።
በ13ኛው ክብረ-በዓል የቦንድ ሳምንት፣ አውደ-ርዕዮች፣ የምስጋና፣ ዕውቅናና ሌሎች የድጋፍ ማሰባሰብ የንቅናቄ መድረክ ዝግጅቶች እንደሚደረጉ ገልፀዋል።
በቀጣይ የንቅናቄ ዝግጅቶችም 300 ሚሊየን ብር ለማሰባሰብ መታቀዱን ተናግረዋል። ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ድጋፋቸውን እንዲያጠናክሩ ጥሪ አቅርበዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!