
የአማራን ሕዝብ በማሠቃየትና ችግር ውስጥ በማስገባት ድል ይገኛል በሚል የእውር ድንበር የትግል ስልት የሚከተለው ፅንፈኛና ዘራፊ ኃይል ሕዝቡን ወደ ተወሳሰበ ስቃይ አስገብቶታል።
ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ ባለፈው የተፈጠረውን ክፍተት አስቀድሞ ለመፍታት መንግሥት ለአርሶ አደሩ የሚልከውን ማዳበሪያ እንዳይደርስ ጉዞውን እያያስተጓጎለና እየዘረፈ ስለመሆኑ ሁሉም የሚያውቀው የእለት ተዕለት ተግብሩ ሆኗል።
በስንት ትግል ከአርሶ አደሩ ደጅ የደረሰውን ማዳበሪያ ደግሞ በነፃ ስለምትወስዱ ከመንግሥት አትውሰዱ በሚል የሀሰት ፕሮፖጋንዳ በማሰራጨት ከፍተኛ ብጥብጥና ፍጅት ለመፍጠር ሙከራዎችን በተለያዩ አካባቢዎች እየፈጠረ ይገኛል።
ሕዝብን ከቀን ወደ ቀን ወደ ተወሳሰበ ችግር ለመክተት አልሞ እየሠራ ያለው ፅንፈኛ ዘራፊ ቡድኑ በለመደው መንገድ የካቲት 26/2016 ዓ/ም እኩለ ቀን አካባቢ ከባሕር ዳር – ደብረታቦር – ንፋስ መውጫ – ጋሸና – አላማጣ የተዘረጋው ባለ 230 ኪሎ ቮልት የከፍተኛ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር በንፋስ መውጫ አካባቢ አንደኛው ፌዝ በመሳሪያ በመምታቱ ከሠዓት በኋላ ጀምሮ አብዛኛው የአማራ ክልል አካባቢ የመብራት አገልግሎት እንዲያጣ አድርጎታል።
ሕዝባችን በቅጡ ያልተሟሉለት በርካታ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ችግሮች ሳይፈቱ በእንቅርት ላይ ጀሮ ደግፍ እንዲሉ የእለት ከእለት ህይወት በመብራት ላይ የተመሠረተውን ሕዝብ ወደ ሌላ የጨለማ ምዕራፍ ጎትቶ በማስገባት የስቃይ ዓይነቶችን እየፈለገ ሲተገብር መዋሉ የቀን ተቀን ተግባሩ ሆኗል።
ይልቅ ሕዝብን እንዲማረር በማድረግ ለትግል የማነሳሳት ዘዴ ያረጀ ያፈጀና ያለፈበትና የተነቃበት የትግል ስልት መሆኑን አልተረዳውም።የሕዝብን ኑሮ በማጎሳቆልና ወደ ድህነት በማስገባት የሚገኝ ድል አይገኝም ቢገኝም እንኳ የትም አያደርስም። በቀጣይም የሕዝብን ስቃይና ምሬት የሚጨምሩ ተግባራትን በመፈፀም መንግሥት እንዲህ አደረገ ለማለት በዝግጅት ላይ እንዳለ መረጃዎች ያሳያሉ።
ስለሆነም ሰላም ወዳዱ ሕዝባችን መሰል ድርጊቶችን ሲያይ ለክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን በስልክ ቁጥር 058-220-13-27 ሪፖርት እንዲያደርግ እና መላው የክልላችን ሕዝብ በውድ የተዘረጋ የሕዝብ ሀብት በዘራፊ ቡድኑ የሚደርስበትን ጥቃት ከፀጥታ ኃይሉ ጋር በመሆን እንዲከላከል የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ያሳውቃል!!!
የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን