የሴቶችን ተጠቃሚነት ማጎልበት የሁልጊዜም ተግባር ሊኾን እንደሚገባ የደሴ ከተማ አሥተዳደር ሴቶች ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ አስታወቀ፡፡

44

ደሴ: የካቲት 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን “ሴቶችን እናብቃ ልማት እና ሰላምን እናረጋግጥ” በሚል መሪ መልእክት በደሴ ከተማ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በተለያዩ ሁነቶች ተከብሯል፡፡

ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን በዓለም ደረጃ ለ113ኛ፣ በሀገር አቀፍ ደግሞ ለ48ኛ ጊዜ ነው እየተከበረ የሚገኘው፡፡ሴቶች ቤተሰብን ከማሥተዳደር ባለፈ በሀገር ግንባታ እና ተሳትፎ ሚናቸው የጎላ መኾኑን በመድረኩ የተገኙት የክፍለ ከተማ ሥራ አሥፈጻሚዎች እና የሴቶች ሊግ አመራር ገልጸዋል፡፡

አመራሮቹ የሴቶች ቀን መከበር ፋይዳው የጎላ መኾኑን ተናግረዋል፡፡የደሴ ከተማ አሥተዳደር ሴቶች ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ ምሳዬ ከድር የሴቶችን ቀን ከማክበር ባለፈ የሴቶችን ተጠቃሚነት ማጎልበት የሁልጊዜም ተግባር እንደኾነ አንስተዋል፡፡ኀላፊዋ ለዚህም ከሴቶች ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ በተጨማሪ የሌሎች ተቋማት ርብርብ ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው ነው የገለጹት፡፡

ዘጋቢ:-ፊኒክስ ሃየሎም

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በአማራ ክልል ከሚስተዋለው የፀጥታ ችግር ቀጥሎ የኑሮ ውድነት የማኅበረሰቡ አንገብጋቢ ችግር ነው” የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ
Next articleባየርን ሙኒክ አሠልጣኝ ዣቢ አሎንሶን ለመቅጠር ድርድር ላይ መኾኑ ተገለጸ።