“በአማራ ክልል ከሚስተዋለው የፀጥታ ችግር ቀጥሎ የኑሮ ውድነት የማኅበረሰቡ አንገብጋቢ ችግር ነው” የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ

26

ደሴ: የካቲት 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በአማራ ክልል ከሚስተዋለው የፀጥታ ችግር ቀጥሎ የኑሮ ውድነት የማኅበረሰቡ አንገብጋቢ ችግር መኾኑን የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ምክትል ኀላፊ በዛብህ ግዛቸው ተናግረዋል።

ቢሮው ባለፉት ስድስት ወራት ያከናወናቸውን ተግባራት በደሴ ከተማ ከባለድርሻ አካላት ጋር ገምግሟል። በውይይት መድረኩ የሁሉም ዞኖች እና ወረዳዎች ፈጻሚ አካላት፣ ኅብረት ሥራ ማኅበራት እንዲሁም በትብብር የሚሠሩ ባለሃብቶች ተገኝተዋል።

በውይይቱ የተሳተፉ ባለሃብቶች ክልሉ የፀጥታ ችግር ውስጥ ቢኾንም ችግሩን በመቋቋም ለማኅበረሰቡ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ሲያቀርቡ መቆየታቸውን ጠቅሰዋል።በቀጣይም ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር በመሥራት በቂ ምርቶችን በማቅረብ የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት እንሠራለን ሲሉ ተናግረዋል።

የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ ኀላፊ ሙሐመድ መኮንን “በገበያው ላይ የሚስተዋለውን የዋጋ ንረት ለማረጋጋት እንደ ዞን ዘርፍ ብዙ ሥራዎች ስንሠራ ቆይተናል” ብለዋል። በየአካባቢው የሚስተዋሉ የፀጥታ ችግሮች ለሥራቸው መጓተት ምክንያት እንደኾኑባቸው በመግለጽ።

የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኀላፊ በዛብህ ግዛቸው በክልሉ ከፀጥታው ጉዳይ በመቀጠል የኑሮ ውድነት የማኅበረሰቡ አንገብጋቢ ችግር መኾኑን አንስተዋል።
ሸማች ተኮር የገበያ ሥርዓትን በመዘርጋት እና ምርትን በበቂ ሁኔታ በማቅረብ በዘርፉ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት እየሠሩ መኾናቸውንም ተናግረዋል።

በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮች በተለይ ደግሞ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ከቦታ ቦታ ለማንቀሳቀስ የፀጥታ ችግር፣ ሕገ ወጥነት፣ የገበያ ቦታ ዕጥረት እንዲሁም ሌሎች ተጓዳኝ ችግሮች ዘርፉ የሚጠበቅበትን አበርክቶ እንዳይወጣ እንቅፋት የኾኑ ጉዳዮች መኾናቸው በውይይቱ ተነስተዋል። በቀጣይ ሸማች ተኮር የገበያ ሥርዓት በመዘርጋት የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት እንደሚሠራም ተጠቁሟል።

ዘጋቢ:- ደምስ አረጋ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በደም የተከበረው በላብና በሕግ ይፀናል” አቶ አሸተ ደምለው
Next articleየሴቶችን ተጠቃሚነት ማጎልበት የሁልጊዜም ተግባር ሊኾን እንደሚገባ የደሴ ከተማ አሥተዳደር ሴቶች ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ አስታወቀ፡፡