“በደም የተከበረው በላብና በሕግ ይፀናል” አቶ አሸተ ደምለው

120

ሁመራ: የካቲት 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ሕዝብ የወልቃይት ጠገዴ አማራ ባለፈው ሥርዓት የደረሰበትን ግፍ እና መከራ በመገንዘብ ከወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ጎን ሊቆም እንደሚገባ የዞኑ ነዋሪዎች ጠይቀዋል።

በዞኑ አሥተዳዳሪ አሸተ ደምለው የተጻፈው “የተከዜ አዳኝ ትውልድ” መጽሐፍ በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን በሁመራ ከተማ ተከዜ ወንዝ ዳርቻ ላይ የዞኑ ሕዝብ በተገኘበት ተመርቋል።

በመጽሐፍ ምረቃ መርሐ ግብሩ የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ወረዳዎች የጠገዴ ወረዳ ቅራቅር፣ የታች አርማጭሆ፣ የምዕራብ ጎንደር ዞን የምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ፣ የምድረ ገነት ከተማ አሥተዳዳሪዎች እና ነዋሪዎች ተሳታፊ ኾነዋል።

በምረቃ መርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ነዋሪዎች ባለፉት ሦስት አስርት ዓመታት የአገዛዝ ዘመን ባሕላቸውን እንዳይገልጹ፣ በቋንቋቸው እንዳይናገሩ፣ በአባቶቻቸው ርስት አርሰው እንዳያመርቱ፣ ማንነታቸው አማራ ነው ብለው እንዳይናገሩ ሲጨፈጨፉ፣ ሲፈናቀሉ እና በጨለማ ግዞት ተጠፍረው ሲሰቃዩ እንደነበር አንስተዋል።

“የተከዜ አዳኝ ትውልድ” መጽሐፍ የወልቃይት ጠገዴን አማራ ሕዝብ እውነተኛ በደል ግፍ እና መከራ የሚያስቃኝ የእውነት እና የፍትሕ ጥያቄውን ከኢትዮጵያ ሕዝብ ባሻገር ለዓለም ሕዝብ የሚያሳይ በእውነት ላይ የተመሰረተ መጽሐፍ ነው ብለዋል።

በወልቃይት ጠገዴ አማራ ሕዝብ ላይ የተፈጸመው ግፍ በመጽሐፍ ታትሞ መቅረቡ የዓለም ሕዝብ ከወልቃይት ጠገዴ አማራ ሕዝብ ጎን እንዲቆም ያስችላል ያሉት ነዋሪዎቹ ከጨለማ ግዞት ተላቀው የነጻነት አየር እየተነፈሱ፣ የአማራነት የባሕል ካባን ተጎናጽፈው በቆሙበት ጊዜ “ከፋኝ” ብለው የታገሉበት የግፍ ጽዋ በእውነተኛ ብዕር በመጽሐፍ ተሰንዶ ለታሪክ በመቀመጡ ደስተኛ ስለመኾናቸው ነው የተናገሩት።

መጽሐፉ በስድስት ምዕራፎች በ214 ገጾች የወልቃይት ጠገዴ አማራ ሕዝብን እውነተኛ የፍትሕ ትግል ለዓለም ሕዝብ ለማሳወቅ መጻፉን አቶ አሸተ ደምለው አሳውቀዋል።
“የተከዜ አዳኝ ትውልድ” መጽሐፍ ዓይነተኛ ተልዕኮ ለነጻነት ፣ ለማንነት በደም የተከፈለን መስዋዕትነት ለማጽናት እና የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት አስጠብቆ ለመዝለቅ የተጻፈ መኾኑን አቶ አሸተ ገልጸዋል።

“በደም የተከበረው በላብና በሕግ ይፀናል” ያሉት አቶ አሸተ መጽሐፉ ከወልቃይት ጠገዴ አማራ ሕዝብ የታሪክ መነሻነት እስከ አሁኑ ትውልድ ያለውን መስዋዕትነት፣ ታሪካዊ ዳራ፣ የነጻነት ተጋድሎ እና መስዋዕትነትን የቀጣይ የትግል አቅጣጫዎች የሚያመላክት ነው ብለዋል።

የወልቃይት ጠገዴ አማራ ሕዝብን የእውነት፣ የፍትሕ እና የርዕትህ ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ መጽሐፉ ዓይነተኛ ሚና ይጫወታል ነው ያሉት።መጽሐፉ ከወልቃይት ጠገዴ አማራ ሕዝብ ባሻገር የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ማስጠበቅ እና ማጽናት ላይ ትኩረት አድርጓል ብለዋል።

ወልቃይት የኢትዮጵያ አንገት በመኾኗ የወልቃይት ጠገዴ አማራ ሕዝብ ለኢትዮጵያ የግዛት ሉዓላዊነት ዘብ እንደሚቆም በመጽሐፉ መካተቱን ገልጸዋል። በምረቃ መርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ እና የሰላምና ጸጥታ መምሪያ ኀላፊ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ “የተከዜ አዳኝ ትውልድ” መጽሐፍ የወልቃይት ጠገዴ አማራ ሕዝብ በጨለማው ዘመን የደረሰበትን መሪር ሀዘን እና መከራ በሚገባ የሰነደ እና የቀጣይ የትግል አቅጣጫን የጠቆመ ነው ብለዋል።

የወልቃይት ጠገዴ አማራ ሕዝብ ማንነቱ ሕጋዊ እውቅና እንዲያገኝ በምክንያት በመደገፍ እና በመቃወም ትግሉ ፍሬ እንዲያፈራ ሊሠራ ይገባል ብለዋል። የወልቃይት ጠገዴ አማራ ሕዝብ አንድ እንጅ ሁለት ሦስት ጥያቄ የለውም፤ “እኛ አማራ ነን” ያሉት ኮሎኔል ደመቀ ጥያቄው እውቅና እንዲያገኝ አንድነትን ይበልጥ ማጠናክር ይገባል ነው ያሉት።

በመርሐ ግብሩ አንድ መጽሐፍ በ950 ሺህ ብር የተሸጠ ሲኾን የማንነት ጥያቄያቸው ሕጋዊ እውቅና እስኪያገኝ በአንድነት እንደሚታገሉም ነዋሪዎቹ ቃል ገብተዋል።

ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleሴቶች በማኅበረሰቡ ዘንድ ያላቸውን ተቀባይነት በመጠቀም ሰላም የማስፈን ኀላፊነታቸውን እንዲወጡ የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ አሳሰበ።
Next article“በአማራ ክልል ከሚስተዋለው የፀጥታ ችግር ቀጥሎ የኑሮ ውድነት የማኅበረሰቡ አንገብጋቢ ችግር ነው” የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ