
ደብረ ማርቆስ: የካቲት 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ሴቶች በማኅበረሰቡ ዘንድ ያላቸውን ተቀባይነት በመጠቀም ሰላም የማስፈን ኀላፊነታቸውን በትጋት እንዲወጡ የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ አሳስቧል።
113ኛው ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን “ሴቶችን እናብቃ ሰላም እና ልማትን እናረጋግጥ” በሚል መሪ መልዕክት በደብረ ማርቆስ ከተማ በፖናል ዉይይት ተከብሯል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር የብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት አደረጃጀት ዘርፍ ኀላፊ ወይዘሮ ላቀች ሰማ ሴቶች ያላቸዉን አቅም በመጠቀም የአካባቢው ማኅበረሰብ በሰላም ወጥቶ እንዲገባ እና ሠርቶ እንዲለወጥ ኀላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።
የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ ወይዘሮ ፈንታነሽ አፈወርቅ በሰላም እጦት ወቅት ሴቶች ይበልጥ ተጎጂ በመኾናቸውን ተናግረዋል።
ዓለም አቀፉ የሴቶች ቀን የሠጣቸዉን መብት እና ኀላፊነት ተጠቅመዉ ግጭት ተወግዶ ሰላም እንዲመጣ የሴቶች ሚና የላቀ ሊሆን እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል። ሠላም የሚጀምረዉ ከራስ እና ከቤተሠብ ነው ያሉት የመድረኩ ተሳታፊዎች በክልሉ የተከሰተው ግጭት እንዲፈታ እና ሰላም እንዲረጋገጥ የድርሻችንን ለመወጣት ቁርጠኛ ነን ብለዋል።
ዓለም አቀፉ የሴቶች ቀን በደብረ ማርቆስ ከተማ ለ29ኛ ጊዜ በፓናል ውይይት ሲከበር ከየክፍለ ከተማው ከሴቶች ሊግ፣ ሴቶች ፌደሬሽን እና ከቤት ሠራተኞች ማኅበር የተውጣጡ ተወካዮች ተሳትፈዋል።
ዘጋቢ:- ቤተልሄም ተስፋየ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!