ከባሕር ዳር – ጋሸና – አላማጣ የተዘረጋው መስመር በመበጠሱ ኃይል መቋረጡን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ።

23

ባሕር ዳር: የካቲት 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ከባሕር ዳር – ደብረታቦር – ንፋስ መውጫ – ጋሸና – አላማጣ የተዘረጋው ባለ 230 ኪሎ ቮልት የከፍተኛ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር በመበጠሱ በአካባቢዎቹ ኃይል መቋረጡን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታውቋል።

በተቋሙ የማስተላለፊያ መስመሮች እና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ኦፕሬሽን ዘርፍ የሰሜን ምዕራብ ሪጅን የኦፕሬሽን እና ጥገና መምሪያ ዳይሬክተር ውበት አቤ ዛሬ ረፋድ ላይ ጀምሮ በንፋስ መውጫ አካባቢ የኃይል ማስተላለፊያ መስመሩ አንደኛው ፌዝ ተበጥሷል ብለዋል።

ይህን ተከትሎም ከንፋስ መውጫ – ጋሸና- አላማጣ – መኾኒ- መቀሌ የሚሄደው መስመር ኃይል መቋረጡን ገልጸዋል።የደረሰውን ጉዳት በአፋጣኝ በመጠገን አገልግሎቱን ለመመለስ እየተሠራ ነው ማለታቸውን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል መረጃ ያመላክታል፡፡

በተመሳሳይ ከደብረ ብርሃን – ሸዋሮቢት – ኮምቦልቻ የተዘረጋው መስመር በሸዋ ሮቢት ከተማ አቅራቢያ በመበጠሱ ከሸዋ ሮቢት እና ከሚሴ ከተሞች በስተቀር አብዛኛዎቹ የሰሜን ምሥራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች ኃይል መቋረጡን የሪጅኑ ዳይሬክተር በድሩ አሕመድ አስታውቀዋል፡፡

ከኮምቦልቻ በባቲ ኃይል ሲያገኙ የነበሩት ሠመራ እና የተለያዩ የአፋር ክልል ዞኖች እና ወረዳዎች እንዲሁም በወልድያ አላማጣ መስመር ኃይል ሲያገኙ የነበሩት መቀሌን ጨምሮ አብዛኛዎቹ የትግራይ ከተሞች ኃይል እንደተቋረጠባቸው ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡ ከትናንት በስቲያ ከሰዓት በኋላ የተበጠሰውን መስመር በመጠገን አገልግሎቱን ለማስቀጠል ርብርብ እየተደረገ መኾኑን ኤፍቢሰ ዘግቧል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየኢትዮጵያ አትሌቲክስ ልዑክ በቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት አቀባበል ተደረገለት።
Next articleሴቶች በማኅበረሰቡ ዘንድ ያላቸውን ተቀባይነት በመጠቀም ሰላም የማስፈን ኀላፊነታቸውን እንዲወጡ የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ አሳሰበ።