
ባሕር ዳር: የካቲት 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በአማራ ክልል በግማሽ በጀት ዓመቱ በተሰራጩ አማራጭ የኃይል ምንጭ ቴክኖሎጂዎች ከ187 ሺህ 800 በላይ የገጠር ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን የክልሉ ውኃ እና ኢነርጂ ቢሮ አስታወቀ።
በክልሉ በሁሉም የገጠር አካባቢዎች አማራጭ የኃይል ምንጭ ቴክኖሎጂ ሙሉ በሙሉ ተደራሽ ለማድረግ የ10 ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ ተይዞ እየተሠራ መኾኑ ተመልክቷል።
የቢሮው ምክትል ኀላፊ ጥላሁን ሽመልስ እንደገለጹት በክልሉ የገጠሩን ነዋሪዎች አማራጭ የኃይል ምንጭ ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ።
ባለፉት ዓመታት በባለድርሻ ተቋማት ቅንጅት የአማራጭ ኃይል ቴክኖሎጂ ተደራሽነትን ለማስፋት ጥረት መደረጉን አውስተዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት ደግሞ 37 ሺህ 564 የተለያዩ አማራጭ የኃይል ምንጭ ቴክኖሎጂን በማመቻቸት 187 ሺህ 800 የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አስታውቀዋል።
ተጠቃሚ የኾኑትም ከ500 በላይ የባዮ ጋዝ ግንባታ እና ከ19 ሺህ በላይ በፀሐይ ኃይል የሚሠራ፤ ቀሪው የማገዶ ቆጣቢ ምድጃዎች በማመቻቸት መኾኑን አመልክተዋል።
አማራጭ የኃይል ምንጭ ቴክኖሎጂ የሴቶችን ጊዜ እና ጉልበት ከመቆጠብ ባሻገር ተረፈ ምርቱ የአርሶ አደሩን ምርታማነት በማሳደግ እና ዘመናዊ አኗኗርን ለመተግበር ባለው ጥቅም በኅብረተሰቡ ዘንድ ተመራጭ እየኾነ መምጣቱን አብራርተዋል።
በቀጣይም ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የኢነርጂ መንደር ምስረታ መርሐ ግብርን ለማስጀመር እንደሚሠራም ጠቁመዋል።
የደቡብ ወሎ ዞን ውኃ እና ኢነርጂ መምሪያ ኀላፊ ጌታቸው ጽጌ በበኩላቸው በግማሽ በጀት ዓመቱ 9 ሺህ 568 የማገዶ ቆጣቢ ምድጃዎች የማሰራጨት እና 79 ባዮ ጋዝ ግንባታ በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ማብቃት መቻሉን ገልጸዋል።
በተጨማሪም ከ1 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች ባዮ ጋዝ እንዲገነባላቸው ጥያቄ ማቅረባቸውን ጠቅሰዋል፤ ከእነዚህም 425 ለመሥራት ጥረት እየተደረገ መኾኑን አስረድተዋል።
አማራጭ የኃይል ቴክኖሎጂ ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት እየተሠራ መኾኑን የገለጹት ደግሞ የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ውኃ እና ኢነርጂ መምሪያ ኀላፊ ብርሃኑ ይመር ናቸው።
በዚህም በግማሽ በጀት ዓመቱ ከ3 ሺህ 600 በላይ የባዮ ጋዝ ግንባታ፣ የማገዶ ቆጣቢ ምድጃ እና በፀሐይ ኃይል የሚሠራ የኃይል አማራጭ ለኅብረተሰቡ መድረሱን ተናግረዋል።
በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ላይ አርማጭሆ ወረዳ ነዋሪ ሲሳይ ቸኮል በሰጡት አስተያየት ባዮ ጋዝ በማስገንባት ለመብራት እና ምግብ ማብሳያነት እየተጠቀሙበት እንደኾነ ገልጸዋል።
የባዮ ጋዝ ተረፈ ምርትንም በአፈር ማዳበሪያነት በመጠቀም ለጓሮ አትክልት እና ለመስኖ ልማት በማዋል ዘርፈ ብዙ ጥቅም እያገኙበት መኾኑን ተናግረዋል።
የማገዶ ቆጣቢ ምድጃ መጠቀማቸው በጭስ ከሚደርስባቸው የዐይን ህመም እና ከማገዶ ወጪ መዳናቸውን የገለጹት በሰሜን ሸዋ ዞን የባሶና ወራና ወረዳ ነዋሪ ወይዘሮ ዓይናለም በቀለ ናቸው። ማገዶ ቆጣቢ ምድጃ መጠቀማቸው ወጪን እንደቆጠበላቸውም ጨምረው ተናግረዋል።
ኢዜአ እንደዘገበው የክልሉ ውኃ እና ኢነርጂ ቢሮ አማራጭ የኃይል ምንጭ ቴክኖሎጂ ስርጭትን በሁሉም የገጠር አካባቢዎች ተደራሽ ለማድረግ የ10 ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ ይዞ እየሠራ መኾኑም ተመላክቷል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!