በአማራ ክልል በሰው ሠራሽ እና በተፈጥሮ አደጋዎች የደረሰውን ችግር በትብብር ለመፍታት ያለመ ምክክር እየተካሄደ ነው።

17

አዲስ አበባ፡ የካቲት 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል በሰው ሠራሽ እና በተፈጥሮ አደጋዎች የደረሰውን የድርቅ እና ሌሎች ጉዳቶችን በትብብር ለመፍታት የአማራ ክልል የገንዘብ ቢሮ ያዘጋጀው የትብብር እና የምክክር መድረክ ነው በአዲስ አበባ እየተካሄደ የሚገኘው።

ምክክሩም “የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ለዘላቂ ልማት እና ለሕዝብ ተጠቃሚነት” በሚል መሪ መልእክት ነው እየተካሄደ ያለው፡፡ በምክክሩ ላይም የክልሉ መንግሥት የሥራ ኀላፊዎች እና አጋር ድርጅቶች ተገኝተዋል።

በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማእረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ እና የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) በአማራ ክልል በደረሰው የሰላም እጦት እና የተፈጥሮ አደጋ ምክንያት ጉዳት መድረሱን ገልጸዋል፡፡ እነዚህን ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች ባለ ድርሻ አካላት ከመንግሥት ጋር በመተባበር ወገኖቻቸውን ሊደግፉ እንደሚገባ ነው ያስገነዘቡት።

ሁሉም አጋር ድርጅቶች እና ሲቪል ማኅበራት እያደረጉ ያለውን ትብብር ሲያጠናክሩ በክልሉ የተጎዱ ወገኖችን ለመደገፍ. የታደሰ አብሮነት እና ሀገራዊ ትስሰርን ለማሳደግ እንደሚረዳም ዶክተር ሙሉነሽ ገልጸዋል፡፡ የድጋፍ መድረኮች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባልም ብለዋል።

የአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ ባዘጋጀው በዚህ የድጋፍ የምክክር መድረክ ላይ በአማራ ክልል በሰው ሠራሽ እና በተፈጥሮ አደጋዎች የደረሱ ጉዳቶች ጥናት ቀርቧል።
በቀረበው ጥናትም በክልሉ በደረሰው አደጋ ምክንያት በሰዎች እና በንብረቶች ላይ ከባድ ጉዳት መድረሱ ተጠቅሷል።

በድርቅ ከተጎዱ ወገኖች በተጨማሪም በጤና፣ በትምህርት ተቋማት እና በተለያዩ የሕዝብ መሥሪያ ቤቶች በሰው ሠራሽ አደጋ ምክንያት ጉዳት መድረሱ በመድረኩ ተጠቅሷል፡፡

ዘጋቢ፡- ራሄል ደምሰው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ሕዝባችን እየገጠመው ካሉ የኢኮኖሚ ልማትና የማኅበራዊ ልማት ስብራቶች ለማውጣት በተለይ የወጣቶች የሥራ እድል ፈጠራ ላይ በትኩረት መሥራት ይጠይቃል” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ
Next articleበአማራ ክልል ከ187 ሺህ 800 በላይ የገጠር ነዋሪዎች አማራጭ የኃይል ምንጭ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ኾኑ