ካራ ማራን ስናስታውስ

65

ባሕር ዳር፡ የካቲት 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ በየዘመናቱ ከውስጥም ከውጭም የማይተኙላት በርካቶች ናቸው፡፡ የዛሬ 46 ዓመታት ወደኋላ በምናብ ብንጓዝ እንኳን በዚህ ወቅት ጦርነት ውስጥ ነበረች፡፡

ኃይልን ፈጣን የመፍትሔ አማራጭ አድርጎ በመጠቀም የሚታሙት የወቅቱ የሀገሪቱ መሪ ኮሎኔል መንሥቱ ኃይለማርያም የሶማሊያውን ፕሬዝዳንት ዚያድ ባሬን ግን አብዝተው ሳይታገሷቸው እንዳልቀሩ ይነገራል፡፡

የሶሻሊስት ሶማሊያ ርዕሰ ብሔር ጀኔራል ዚያድ ባሬ ታላቋን የሶማሊያ ሪፐብሊክ ለመመሥረት “ድንበራችን እስከ አዋሽ ይዘልቃል” ሲሉ በተደጋጋሚ ተደመጡ፡፡ ራዕያቸውን ዕውን ለማድረግም በድንበር፣ በባሕል፣ በእሴት እና በማንነት የሚቀርባቸውን ወንድም የኢትዮጵያ ሕዝብ ሊወጉ ጦር አሰልፈው ክተት ሠራዊት ምታ ነጋሪት ብለው ጦርነት አዘመቱ፡፡

ከሐምሌ 1969 ዓ.ም እስከ የካቲት 1970 ዓ.ም ምሥራቃዊዋ የኢትዮጵያ ክፍል ኦጋዴን ለፍልሚያ ታጨች፡፡ እጅግ ሞቃታማ የሆነው የኦጋዴን አካባቢ የኢትዮጵያ ጠረፍ የጎረቤት ሀገር ሶማሊያ ደግሞ አዋሳኝ ድንበር ነው፡፡

ሶማሊያን ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ የመሩት ጀኔራል ዚያድ ባሬ ኦጋዴንን በመጠቅለል ታላቋን ሶማሊያ የመመሥረት የቆየ ራዕይ እንደነበራቸው ይነገራል፡፡ ጊዜ አይተው እና ወቅትን ገምተው ኢትዮጵያ በገንጣይ አስገንጣዮች ትግል የተዳከመች ሲመስላቸው እቅዳቸውን ገቢር ለማድረግ ዳዳቸው፡፡

ፕሬዝዳንት ባሬ ያሰቡትን ዳር ለማድረስ ያልደገፉት የኢትዮጵያ ጠላት፤ ያልተጠቀሙበት የሴራ መንገድ አልነበረም፡፡ ሶማሊያ በ1969 ዓ.ም በኢትዮጵያ ላይ ግልፅ ወረራ ከመፈጸሟ በፊት በህቡዕ ተደጋጋሚ ጥቃት በመሰንዘር የኢትዮጵያን የመከላከያ ኃይል ማዳከም ነበር፡፡ ጦርነቱ በግልፅ በታወጀበት 1969 ዓ.ም ሐምሌ ወር ጀምሮ ባሉት ተከታታይ ሳምንታት የሶማሊያ ጦር ባልታሰበ መልኩ ጥቃት ሰንዝሮ ጅግጅጋ፣ ሐረር እና ድሬድዋ ድረስ ዘልቆ ገባ፡፡

በመጀመሪያ በሶብየት ኅብረት እና በመቀጠልም ደግሞ በአሜሪካ ልዩ ድጋፍ የነበረው የፕሬዝዳንት ዚያድ ባሬ ጦር ለድል የተቃረበ መሰለ፡፡ የኋላ ኋላ የውጭ ድጋፍ እየቀነሰበት የመጣው የሶማሊያ ጦር የኢትዮጵያ የውስጥ ተገንጣይ ኃይሎች የውስጥ ለውስጥ ድጋፍ ስላልተለየው ጦርነቱን ከመግፋት አልተቆጠበም ነበር፡፡

የፕሬዝዳንት መንግሥቱ ኃይለማርያም ጦር ወደ ፍጹማዊ ማጥቃት እና እልህ አስጨራሽ ጦርነት መግባቱን የሚያመላክቱ እርምጃዎች መታየት ጀመሩ፡፡ ከኦጋዴን ሞቃታማ ቦታዎች በአንዱ ‹‹ካራማራ›› ከምድርም ከሰማይም እሳት የሚተፉ የጦር አረሮች ምድሪቱን ዘነቡባት፡፡

ታላቋን ሶማሊያ የመመሥረት ራዕዩ ጫፍ የደረሰ የሚመስለው ፕሬዝዳንት ዚያድ ባሬ በመጨረሻም በዚች ዓለም ላይ ምንም ቋሚ የሆነ ነገር የለም ለማለት ተገደደ፤ የዚያድ ባሬ ጦር ድል ተመታ፡፡

ኢትዮጵያ በልጆቿ ታፍራ እና ተከብራ ትኖር ዘንድ ልምድ አላት እና ራሷን በብቃት ተከላከለች፡፡ ታላቅ ለመኾን የታቀደላት ሶማሊያም በማያባራ ጦርነት ውስጥ ገብታ ፈራረሰች፤ ዜጎቿም ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ያላቋረጠ ስደትን አስተናገዱ፡፡

የካቲት 26/1970 ዓ.ም የኢትዮጵያ ጦር፣ የእናት ሀገር ወዶ ዘማቾች እና 16 ሺህ የሚደርሱ የፕሬዝዳንት ፊደል ካስትሮዋ ኩባ አጋር ወታደሮች ይህን ታሪካዊ ጦር ተቀላቅለው የዚያድ ባሬን ጦር ድባቅ መትተው የኢትዮጵያን አሸናፊነት አወጁ፡፡

የማያልፍ የለም፤ ጠብም ፍቅርም ያልፋል፡፡ ለሚያልፍ ሥልጣን እና ሃሳብ የሰው ሕይወት ማስከፈል ግን ተገቢ አልነበረም፤ ዚያድ ባሬ ከ46 ዓመታት በፊት ሺዎች እንዲቀጠፉ እልፎች በከንቱ እንዲያልፉ ምክንያት ነበሩ፡፡ ድርጊታቸው ግን እርሳቸውን ጨምሮ ማንንም አልጠቀመም፡፡

ምንጭ፡- አፍሪካ ፎከስ እና የገብሩ ታሪክ ጥናት

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ለውጥማ አሁን ነው…”
Next article“የካራማራ ድል ሉዓላዊነትን ለማስከበር ዋጋ የተከፈለበት ታላቅ ድል ነው” የቀድሞ ጦር ሠራዊት አባላት