
ባሕር ዳር: የካቲት 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በአማራ ክልል በተያዘው በጀት ዓመት 144 ሺህ 793 ሄክታር መሬት በስንዴ ሰብል ተሸፍኗል፡፡
የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በሥፋት ከተጀመረ ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ በሽፋን እና ምርታማነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን የግብርና ቢሮ መረጃ ያሳያል። የበርካታ አርሶ አደሮች ሕይወትም እየተሻሻለ ይገኛል።
አርሶ አደር ተመስገን ጥላሁን ይባላሉ፡፡ በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር አየሁ ጓጉሳ ወረዳ ነዋሪ ናቸው፡፡ አርሶ አደር ተመሥገን በበጋ ስንዴ ማምረት ከጀመሩ ዓመታትን አስቆጥረዋል፡፡ በልፋታቸው ልክ ማግኘት የጀመሩ ግን የግብርና ባለሙያን ምክረ ሃሳብ መስማት ከጀመሩ ወዲህ ነው፡፡
አርሶ አደር ተመስገን ከሁለት ዓመት ወዲህ የበጋ መስኖ ስንዴ ሲያለሙ የግብርና ምክረ ሃሳብ ተግባራዊ ማድረግ ጀምረዋል፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታት ሁለት ሄክታር የሚጠጋ መሬት በዘር በመሸፈን ከ70 ኩንታል በላይ ስንዴ ማምረት መቻላቸውን ነግረውናል፡፡
ምርጥ ዘር እና ማዳበሪያ በመጠቀም በሄክታር እስከ 35 ኩንታል ማግኘት እንደሚቻልም አንስተዋል፡፡ ይህም “የምርት ማሳደጊያ ግብዓት እና የግብርና ምክረ ሃሳብ በአግባቡ በመጠቀሜ የመጣ ለውጥ ነው” ይላሉ፡፡ ምርታቸው ከነበረው በእጥፍ ማደጉን በመግለጽ፡፡
አርሶ አደር ተመሥገን ስንዴ በበጋ በማምረታቸው ቤተሰባቸው እንጀራ ብቻ ከመመገብ ወጥቶ ዳቦ እና ከስንዴ የተለያዩ የምግብ ዓይነቶችን በማዘጋጀት መመገብ መጀመራቸውን ገልጸዋል።
ከገቢ አንጻርም ስንዴ የተሻለ ዋጋ እያወጣ በመኾኑ ገቢያቸው መጨመሩን ተናግረዋል፡፡ “ለውጥ እማ አሁን ነው ትርፍ አምርቶ አክርሞ መሸጥ ሲመጣ” ብለዋል፡፡
በዚህ ዓመትም የበቆሎ ሰብልን በማንሳት ማሣቸውን በበጋ ስንዴ ሸፍነዋል። ይሁን እንጅ በክልሉ በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ምርጥ ዘር እና ማዳበሪያ በተመጣጣኝ ዋጋ እና በወቅቱ እንዳያገኙ እንቅፋት ቢፈጥርባቸውም ተቋቁመው ማለፋቸውን አንስተዋል፡፡ ስንዴን የግብርናን ምክረ ሃሳብ ተከትሎ መዝራት ከተቻለ ውጤቱ ጥሩ ነው በክረምት ከምናለማው የተሻለ እናገኛለን ብለዋል፡፡
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የመስኖ ባለሙያው ተሻለ አይናለም በ2016 ዓ.ም 250 ሺህ ሄክታር መሬት በስንዴ በመሸፈን 9 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት መታቀዱን ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጅ በክልሉ በተከሰተው የፀጥታ ችግር ምክንያት እስከ አሁን የተሸፈነው መሬት 106 ሺህ 500 ሄክታር መሬት ብቻ ነው ብለዋል። 316 ሺህ 841 አርሶ አደሮች ተሳትፈዋል ነው ያሉት።
እስከ አሁን 290 ሺህ 559 ኩንታል ማዳበሪያ እና ምርጥ ዘርም ጥቅም ላይ ውላል። በዚህ ዓመት የግብዓት ችግር ባይኖርም በፀጥታው ችግር ምክንያት የግብርና ባለሙያው እና የተቋማት የሥራ ኀላፊዎች ድጋፍ ባለማድረጋቸው ምክንያት የታቀደው መሬት በስንዴ መሸፈን አልተቻለም ብለዋል።
በአንድ ማዕከል የሚገኘውን ግብዓት ወደ ተለያዩ አካባቢዎች ለማሰራጨት አለመቻሉን አንስተዋል፡፡ አርሶ አደሮችም ወደ እርሻ ቦታቸው ገብተው እንዳይሠሩ እንቅፋት ቢኾንም በተፈጠረው አንጻራዊ ሰላም ሁሉም ወደ ሥራ መግባቱን ገልጸዋል፡፡
አሁን ላይ አንጻራዊ ሰላም በሰፈነባቸው አካባቢዎች የክረምቱ ዝናብ ዘገይቶ በሚገባባቸው ቦታዎች የሁለተኛ ዙር ስንዴ ልማት ለማልማት እየተሠራ እንደኾነው አንስተዋል።
👉 በአማራ ክልል የበጋ ስንዴ ከተጀመረ ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ የስንዴ ልማት በሽፋን እና በምርታማነት እየተሻሻለ ይገኛል።
በዚህም፦
👉 በ2013 ዓ.ም 50 ሺህ 200 ሄክታር መሬት ለማልማት ታቅዶ ከ13 ሺህ 231 ሄክታር በላይ መሬት ማልማት ተችሏል። በዚህም 481 ሺህ 700 በላይ ኩንታል ስንዴ ተገኝቷል።
👉 በ2014 ዓ.ም 80 ሺህ ሄክታር መሬት ለማልማት ታቅዶ ከ40 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ማልማት ተችሏል። በዚህም 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ተገኝቷል።
👉 በ2015 ዓ.ም 250 ሺህ ሄክታር መሬት በማልማት 10 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ለማግኘት ታቅዶ ከ213 ሺህ 500 ሄክታር በላይ መሬት በዘር በመሸፈን 7 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል ምርትም ተገኝቷል። 298 ሺህ 150 ኩንታል ምርጥ ዘር፣ 290 ሺህ ኩንታል ማዳበሪያ ጥቅም ላይ ውሏል። 270 ሺህ 523 አርሶ አደሮች ተሳትፈዋል። የተገኘው ምርትም ባለፉት ዓመታት ከተገኘው ምርት የተሻለ እንደነበር አንስተዋል።
👉 በ2016 ዓ.ም 250 ሺህ ሄክታር መሬት በዘር በመሸፈን 9 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማምረት ታቅዷል እስከ አሁንም 144 ሺህ 793 ሄክታር መሬት በስንዴ ሰብል ተሸፍኗል፡፡ 190 ሺህ 150 ኩንታል ምርጥ ዘር፣ 303 ሺህ 451 ኩንታል ማዳበሪያ ጥቅም ላይ ውሏል። 452 ሺህ 897 አርሶ አደሮች ተሳትፈዋል።
አቶ ተሻለ ስንዴን በመስኖ ለማልማት እየተደረገ ያለው ጥረት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡ አርሶ አደሮች በየዓመቱ ባገኙት ውጤት ከነበረባቸው የተሳሳተ አመለካከት ወጥተው ሥራውን በውጤታማነት እየሠሩት መኾኑንም ግምገማዎች እንደሚያሳዩ አብራርተዋል፡፡
ቢሮው የተለያዩ መድረኮችን በመዘጋጀት ከአርሶ አደሮች እስከ ባለሙያዎች ባሰረፀው ግንዛቤ ለውጥ እየመጣ መኾኑን ጠቁመዋል፡፡ሥንዴ ማምረት የሞት የሽረት ጉዳይ መኾኑንም በጋራ ተስማምቶ ወደ ሥራ የተገባበት እንደኾነም ጠቁመዋል፡፡
በዚህ ዓመት በተፈጠረው የፀጥታ ጉዳዩ የፈጠረው ሳንካ በወቅቱ ግብዓት ማድረስ ባለመቻሉ አርሶ አደሮች ለገበያ ይኾነናል ያሉትን ሰብል መዝራታቸውን የጠቆሙት ባለሙያው የመስኖ መሬት ወይም ውኃ ገብ መሬት ጦም አላደረም በተለያዩ ገበያ መር በኾኑ ሰብሎች መሸፈኑንም አያይዘው ጠቁመዋል፡፡አቶ ተሻለ ዘግይቶ ክረምቱ በሚገባባቸው አካባቢዎችም በሁለተኛው ዙር መሥኖ ላይ ስንዴ ለማምረት ጥረት እየተደረገ መኾኑን ጠቁመዋል፡፡
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!