የጋብቻ ውል እና የሕግ ዕይታው

206

ባሕር ዳር: የካቲት 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ባለታሪኮቻችን በቀለ ደጀን እና አበባ ተክሌ ናቸው።

ሁለቱ ባለታሪኮች በድንገት ይተዋወቃሉ። እየዋለ እያደረ ደግሞ በጣም ተቀራረቡ። አበባ ዘመናዊ ቤት፣ መኪኖች እና የንግድ ድርጅትም አላት። በቀለ በወቅቱ ከ50 ሺህ ብር ውጭ ምንም ዓይነት ሃብት እና ንብረት አልነበረውም።

የበቀለ እና አበባ ግንኙነት እየዋለ እያደረ ሲሄድ ወደ ፍቅር ያድጋል። በመቀጠልም በአንድ ቤት መኖርም ጀመሩ። ይህ ሲኾን በበቀለ እና አበባ መካከል ከልብ ከመነጨ ፍቅር እና እምነት ውጭ ምንም ዓይነት የጋብቻ ውል አልነበረም።

ስለንብረት ጉዳይም ያላቸውን ሃብት በጋራ ከመጠቀም እና ተጨማሪ ለማፍራት በጋራ ከመጣር የዘለለ የተዋዋሉት ምንም ውል የለም። እምነት እና ፍቅር ብቻ!
ልብ በሉ! አበባ መኪና፣ ቤት እና ሌላም ሃብት እና ንብረት አላት። በቀለ ደግሞ ሠርቶ የቋጠራትን 50 ሺህ ብር ይዞ ነው የግሌ የሚሉት ነገር ሳይኖራቸው በሚያስቀና ፍቅር በአንድ ላይ መኖር የጀመሩት። አምስት የደስታ ዓመታትን በጋራ አሳለፉ።

በፍጹም እምነት እና ፍቅር ላይ ብቻ የተመሰረተው የአበባ እና የበቀለ ኑሮ ከአምስት ዓመታት በላይ አልዘለቀም። በፍቅር ውስጥ ጠብ እና ጭቅጭቅ ተፈጠረ። እየዋለ እያደረ ጭቅጭቁ በረታ፤ የመለያየት ፍላጎትም ከሁለቱም በኩል እያየለ መጣ።

የአበባ ፍላጎት እና ክርክር በቀለ በፊትም የነበረውን ሃብቶ ይዞ እንዲለያዩ ነው። የበቀለ ፍላጎት እና ክርክር ደግሞ ንብረታቸው በሙሉ እኩል መካፈል ነው።
የአበባ እና የበቀለ የመለያየት ሂደት ምን መልክ ይኖረዋል? በእንዲህ መሰል ጉዳይ ላይ ስለንብረት ክፍፍል ሂደቱስ ሕጉ ምን ይላል? ይህንን እና ተጨማሪ ማብራሪያዎችን ከፌዴራል የቤተሰብ ሕግ ጋር እያጣቀስን ቀጥለን እንመለከታለን።

ትዳር ትልቅ ማኅበራዊ ተቋም ነው። መልካም በኾነ ትዳር የሚመራ ቤት እና ቤተሰብ ለሀገር ጠቃሚ የኾነ ትውልድ ለማፍራት መሠረትም ነው። ስለዚህ ትዳር እውነትም ትልቅ ተቋም በመኾኑ በአግባቡ ተመስርቶ በሥርዓት መመራት አለበት። የታሰበው አልኾን ሲልም በሕግ እና በአግባቡ ነው ተጋቢዎች መለያየት ያለባቸው።

በፌዴራሉ የቤተሰብ ሕግ አዋጅ ቁጥር 213/1992 ከአንቀጽ 2 እስከ 4 የተጠቀሱ ድንጋጌዎች እንደሚያሳዩን ጋብቻ የሚፈጸመው በሦስት አማራጮች ነው።
እነሱም በባሕላዊ ሥነ ሥርዓት፣ በሃይማኖት እና በክብር መዝገብ ሹም ፊት (በወሳኝ ኩነት ተመዝግቦ ሰርተፊኬት የሚሰጠው) ናቸው። በጥንዶች መካከል የተደረገው የትዳር ግንኙነት በሕግ እውቅና የሚሰጠው ከሦስቱ የጋብቻ መፈጸሚያ አማሯጮች ውስጥ በአንዱ የተፈጸመ ከኾነ ብቻ ነው።

የበቀለ እና አበባ ግንኙነት ግን የሕግ እውቅና ከሚያሰጡት ከሦስቱም የጋብቻ መፈጸሚያ መንገዶች ውጭ ነው። የፌዴራል የቤተሰብ ሕግ በምዕራፍ 7 አንቀጽ 98 እንዲህ አይነቱን ግንኙነት “እንደ ባል እና ሚስት አብሮ መኖር” ሲል ይገልጸዋል። ትርጓሜውም “አንድ ወንድ እና አንዲት ሴት በሕግ በሚጸና አኳኋን ጋብቻ ሳይፈጽሙ በትዳር መልክ የኖሩ ሲኾን ነው” ተብሎ ተብራርቷል።

በሕግ የጸናን ጋብቻ ተጋቢዎች እንደፈለጉ የማቋረጥ ሥልጣን የላቸውም። ጋብቻው የሚፈርስበት በሕጉ የተቀመጠ ሂደት አለው። ስለዚህ ሂደቱን ተከትሎ ፍርድ ቤት ሲፈቅድ ብቻ ነው ሕጋዊ ትዳር ሊፈርስ የሚችለው።

የበቀለ እና አበባ ግንኙነት ግን በሕግ እውቅና የተሰጠው ባለመኾኑ ራሳቸው በፈለጉበት ጊዜ ሁሉ ሊያቋርጡት ይችላሉ። የቤተሰብ ሕጉ ምዕራፍ 7 አንቀጽ 105 ላይ “እንደ ባልና ሚስት አብረው የሚኖሩ ጥንዶች በማንኛውም ጊዜ ግንኙነታቸውን እንዲቋረጥ ማድረግ ይችላሉ” ሲል አስቀምጦታልና።

ባለታሪኮቻችን ግንኙነታቸውን በፈቃዳቸው መተው ከቻሉ የንብረት ክፍፍል ሂደቱ ደግሞ እንዴት ሊኾን እንደሚችልም እንመልከት።
ሕጋዊ ጋብቻ ሳይፈጽሙ እንደ ባል እና ሚስት አብረው የሚኖሩ ወንድ እና ሴት ከሦስት ዓመት ላላነሰ ጊዜ አብረው ከኖሩ ንብረቶቻቸው የጋራ ሃብታቸው እንደሚኾን በቤተሰብ ሕጉ ምዕራፍ 7 አንቀጽ 102 ላይ በግልጽ ተቀምጧል። የተለየ ውል ወይም ማስረጃ ካልቀረበ በስተቀር ንብረቶቻቸው በግንኙነት ውስጥ የተፈሩ ተደርገው እንደሚቆጠሩም እዚሁ ላይ ተደንግጓል።

ባለታሪኮቻችን ምንም አይነት ውል የላቸውም። ሕጉ ከሚያስቀምጠው የሦስት ዓመታት የጊዜ ገደብ በላይም አብረው ኖረዋል። ስለዚህ የአበባ ቤት እና መኪና፣ በቀለ ይዞት የገባው አነስተኛ ጥሬ ገንዘብ እና ከተገናኙ በኃላ በጋራ ያፈሩት ንብረት ጭምር የጋራ ሃብታቸው ስለመኾኑ ሕጉ ያስረዳል።

ይህ ማለት ደግሞ በአበባ በኩል የተለየ የመከራከሪያ ማስረጃ እስካልመጣ ድረስ ከአምስት ዓመት በፊት 50 ሺህ ብር ይዞ ከአበባ ጋር ግንኙነት የፈጠረው በቀለ ዛሬ ላይ ቤት፣ መኪና እና ሌሎች ንብረቶችን የመካፈል መብት አለው ማለት ነው።

ከዚህ የምንረዳው በሕግ ክፍተት ምክንያት የሚገባንን ጥቅም እንዳናጣ ወይም ደግሞ አልባሌ የንብረት ኪሳራ እንዳይደርስብን ንቃተ ሕግ ሊኖረን ይገባል የሚለውን ነው።
አበባ የግል ንብረቷን የሚያሳውቅ ስምምነት መዋዋል ግድ ይላት ነበር። የቤተሰብ እና የሀገር መሠረት የኾነውን ጋብቻ በሕግ ፊት የጸና እንዲሆን በሚያስችል ውል መመሥረት እና በአግባቡ መምራት እንደሚገባ የዕለቱ መልእክታችን ነው።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በእልህ ግጭትን ከማባባስ ይልቅ ተወያይቶ ችግሮችን መፍታት ዘላቂ መፍትሔን ያመጣል” የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት
Next article“ለውጥማ አሁን ነው…”