“በእልህ ግጭትን ከማባባስ ይልቅ ተወያይቶ ችግሮችን መፍታት ዘላቂ መፍትሔን ያመጣል” የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት

53

ባሕር ዳር: የካቲት 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በሰብዓዊ መብት፣ በግጭት አፈታት፣ በሰላም፣ በመልካም አሥተዳደር፣ በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ እና በመሳሰሉት ዘርፎች ላይ እንዳይሠሩ የሕግ ክልከላ እና ቅድመ ሁኔታ ተደርጎባቸው ቆይቷል።

በቅርቡም የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ላይ የሚኖራቸውን ሚና ለማጎልበት በሙሉ አቅማቸው እንዲሠሩ ለማስቻል አዋጅ ቁጥር 1113/2011 ዓ.ም ተደንግጎ ሥራ ላይ ውሏል።

አሁን ላይ በኢትዮጵያ እያጋጠሙ ያሉ የግጭት እና የሰላም እጦት ችግሮችን ለመፍታት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ከመንግሥት እና ከሕዝቡ ጋር እየሠሩ መኾኑን የፕሮ ዴቨሎፕመንት ኔትወርክ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር እና የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት አሕመድ ሁሴን ገልጸዋል።

ፕሬዚዳንቱ በኢትዮጵያ 5 ሺህ የሲቪል ሶሳይቲ ድርጅቶች መኖራቸውን ጠቅሰዋል። ድርጅቶቹ ከልማት ሥራዎች በተጨማሪም በግጭት አፈታት፣ በሰላም፣ በመልካም አሥተዳደር፣ በሰብዓዊ መብቶች እና በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ላይ እንደሚሠሩ ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የሚታዩ ግጭቶች እና የሰላም መደፍረስ ምክንያቱ የዴሞክራሲ ባሕል ልምምድ አነስተኛ መኾኑ ነው ያሉት አቶ አሕመድ በሥርዓት ለውጥ ጊዜ የቀድሞውን በሙሉ አጥፍቶ እንደ አዲስ መጀመር የተለመደ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ ይህም የዴሞክራሲ ባሕል ግንባታው የሚቀረው ነገር መኖሩንም ጠቁመዋል፡፡

አሁን የሚታየው ሕዝቦች ታፍነውበት የነበረውን አጀንዳ ሁሉ ወደ አደባባይ ማውጣታቸውን ነው ያሉት አቶ አህመድ ነገር ግን በምን መልኩ እንደሚጠየቅ እና እንደሚስተናገድ በማወቅ በኩል ውስንቶች እንደሚስተዋሉ ገልጸዋል። ጥያቄዎቻችን አይፈቱም የሚል ተስፋ ቆራጭነት በጥያቄዎቹ ላይ ከመወያየት ይልቅ ሌሎች የመጡበትን መንገድ ለመከተል መፈለግን ሌላው ችግር ኾኗል ብለዋል።

”ሌሎች ሀገራትም ተመሳሳይ ችግር ውስጥ ገብተው እንደነበር እናስተውላለን” የሚሉት ምክትል ፕሬዚዳንቱ በኢትዮጵያ ችግሮች የተባባሱት በለውጡ ስም ሁሉም ያሰበውን ለማሳካት ሩጫዎች መብዛታቸው እንደኾነም ገልጸዋል። ነገር ግን ያልተገባው ሩጫ በሀገር ላይ የሚያመጣው መዘዝ እንዳለው ማሰብ እንደሚገባም አሳስበዋል። ይህም ከግጭት አልፎ ወደ ጦርነት እያደገ፤ ጦርነቱም ሌሎች ያልተጠበቁ ችግሮች እየፈጠረብን ነው። አንዱ አንዱን እየወለደ በግጭት አዙሪት ውስጥ እንድንገኝ አድርጎናል ብለዋል።

”የግጭት መንስኤዎችን በመጀመሪያ ከአእምሯችን ነው ማስወገድ ያለብን” ያሉት አቶ አሕመድ የሃሳብ ልዩነቶችን በመቻቻልና በውይይት መፍታት መልመድ አለብን ብለዋል። እልህ መጋባት ለችግር ቅርብ ያደርገናል ብለዋል። ችግሮችን በግጭት ለመፍታት መፈለግ ሃሳቦቻችን እና ጥያቄዎቻችን ለሌሎች ለማስገንዘብ ያስቸግረናል፡፡ ባለፉት ዘመናት ከመመካከር ይልቅ መሸናነፍን ብቻ ለምደን ስለቆየን ነው አሁን እየተጋጨን ያለነው ሲሉም የግጭት አፈታት ያለፈ ታሪካችን ደካማነት አመላክተዋል።

ጥያቄ ያላቸው አካላት ጥያቄዎቻቸውን አንጥረው ለይተው በግልጽ መጠየቅ እንዳለባቸው አቶ አሕመድ ጠቁመዋል። ”በእልህ ግጭትን ከማባባስ ይልቅ ተወያይቶ ችግሮችን መፍታት ዘላቂ መፍትሄ ነው” ብለዋል። ሀገራዊ ጉዳዮች በአንድ አካል ብቻ የሚወሰኑ ሳይኾኑ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች እና ወካይ ተቋሞቻቸው በተሳተፉበት ሁኔታ ውይይት እንዲደረግባቸው እንደሚያስፈልግ ነው የገለጹት።

ለዚህም የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ለፖለቲካ ችግሮች መፍትሄ ለማበጀት፣ የሚከሰቱ ችግሮችን ተወያይቶ የመፍታት አዲስ ባህል ለመገንባት ሁነኛ ተቋም መኾኑን አመላክተዋል። ሁሉም የየራሱ ጥያቄ እንዳለው እና ”ችግሮች የሚፈቱት በምክክር ስለኾነ በምክክር ኮሚሽኑ ንቁ ተሳትፎ ማድረግ እንደሚገባ” አሳስበዋል።

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ አሠራር ለኛ ሀገር አዲስ ይሁን እንጂ ችግሮችን ተወያይቶ ለመግባባት እና ዘላቂ መፍትሄ እንደኾነ እምነታቸውን ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤትም እገዛ ለማድረግ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለውም ተናግረዋል። ”ግጭት ባለበት ሁኔታ ውይይት ማድረግ ስለማይቻል ግጭት እንዲቆም ሲቪል ማኅበራቱ ጥረት ማድረግ እንዳለባቸው” ነው አቶ አሕመድ ያሳሰቡት፡፡

የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን ሥራን እንደቀላል በማየት እድሉን ማጣት እንደማይገባ ያሳሰቡት አቶ አሕመድ ሥራው ለኮሚሽኑ አባላት ብቻ የሚተው አለመኾኑን ነው አጽዕኖት የሰጡት፡፡ ስለኾነም መንግሥት፣ ሚዲያው፣ ሲቪል ማኅበራት እና ሌላውም ሊረባረብ እንደሚገባ አብራርተዋል። ይልቁንም ሌሎች ”ባለድርሻ አካላት ማገዝ እና ተልዕኮውን ውጤታማ ማድረግ ነው የሚጠበቅብን” ብለዋል። ለግጭቶቹ መነሻ ምክንያቶችን በመለየት ተመካክሮ ከእልባቱ ለመድረስ ያግዛል፡፡ ማኅበረሰቡም የኔ የሚላቸውን አጀንዳዎች በማስያዝ እና በመወያየት የድርሻውን መወጣት አለበት ብለዋል።

የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን ተልዕኮ እንዲሳካ በመንግሥት ትከሻ ላይ ብቻ የሚጣል አለመኾኑን ነው አቶ አሕመድ የገለጹት፡፡ ሁሉም አካላት ምክክሩን ካልተገባ ጣልቃ ገብነት እና ጫና ነጻ በማድረግ ኀላፊነታቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋልም ብለዋል፡፡ ግጭቶችን በማብረድና ለውይይቱ ምቹ ሁኔታ መፍጠር እንደሚጠበቅም ጠቅሰዋል። ሰላም በሌለበት ሰርቶ ማደግ ስለማይኖር ለሰላም መስፈን የባለሃብቶችን ድርሻ ከፍተኛነት አንስተዋል፡፡

የሲቪል ሶሳይቲ ድርጅቶች የተከሰተው ግጭት ወደ ጦርነት ከማደጉ በፊት እና በከፋ ጦርነት ውስጥ ለመሥራት ከመቸገር አስቀድመን ከተለያዩ አካላት ጋር በመነጋገር እየሠራን ቆይተናል፤ አሁንም እንሠራለን ብለዋል። የሲቪል ሶሳይቲ ድርጅቶች በብሔራዊ የምክክር ኮሚሽን ረቂቅ አዋጁ ውይይት ላይ ተሳትፈናል ብለዋል።

በቀጣይም በሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ ለመወያየት እና የማያግባቡ ጉዳዮች ላይም በሰላማዊ መንገድ መቻቻል እንደሚያስፈልግ አምነን እየሠራን ነው ብለዋል፡፡ የግጭቱ ተዋናዮች የማኅበረሰቡ ልጆች በመኾናቸው ሲቪል ማኅበራቱ የሕዝብን እና የሀገርን ተጠቃሚነት ለማስፈን ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ መፍታት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ዋሴ ባየ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየላሊበላ-ሙጃ – ቆቦ የኮንክሪት አስፖልት መንገድ ሥራ በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ ድጋፍ እና ክትትል እየተደረገ መኾኑን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአካባቢው ተወካይ ገለጹ፡፡
Next articleየጋብቻ ውል እና የሕግ ዕይታው