የላሊበላ-ሙጃ – ቆቦ የኮንክሪት አስፖልት መንገድ ሥራ በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ ድጋፍ እና ክትትል እየተደረገ መኾኑን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአካባቢው ተወካይ ገለጹ፡፡

24

ባሕር ዳር: የካቲት 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቡግና ምርጫ ጣቢያ ተወካይ ቅድስት አርዓያ፣ የአካባቢው ነዋሪዎች እና የመንገድ ሥራው ተቋራጭ የመንገድ ፕሮጀክቱን የሥራ እንቅስቃሴን ተዘዋውረው ተመልክተዋል፡፡

የቻይና ሲቪል ኢንጅነሪንግ ኮንሰትራክሽን ኮርፖሬሽን ሥራ አሥኪያጅ ሚስተር ሊዮ የላስታ ወረዳ እና የአካባቢው ነዋሪዎች የመንገድ ፕሮጀክቱ በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ እያደረጉት ያለውን ትብብር አድንቀዋል፡፡ ትብብራቸው ቀጣይነት እንዲኖረውም አሳስበዋል፡፡

የመንገድ ሥራውን የሚከታተለው የቤዛ አማካሪ ተጠሪ መሐንዲስ ሞላ አድማሱ የመንገድ ፕሮጀክቱን በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ ለማጠናቀቅ እየሠሩ መኾኑን ተናግረዋል፡፡

የአካባቢው ነዋሪ አቶ ይህነው አቸናፊ የመንገድ ሥራው የረጅም ጊዜ ጥያቄያቸው እንደነበር ገልጸዋል፡፡ ለመንገዱ ሥራ የሚጠበቅባቸውን ሁሉ እያደረጉ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡

የላስታ ወረዳ አሥተዳዳሪ ጌታቸው መልሴ አካባቢው በጸጥታ ችግር ውስጥ ቢኾንም የመንገድ ሥራው እንዳይቆም ኅብረተሰቡ በቀጣይም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቡግና ምርጫ ጣቢያ ተወካይ ቅድስት አርዓያ የመንገድ ሥራው የኅብረተሰቡ የ30 ዓመት ጥያቄ በመኾኑ በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ ድጋፍ እና ክትትል እየተደረገ መኾኑን ጠቁመዋል፡፡ የፌዴራል መንግሥትም ትኩረት ሰጥቶ እንዲሠራ የበኩላቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል፡፡

ኅብረተሰቡ ለመንገድ ሥራው የሚያደርገውን አስተዋጽኦ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ማሳሰባቸውን የላስታ ወረዳ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጽሕፈት ቤት መረጃ ያመለክታል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየጎንደር ከተማ አሥተዳደር የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ በመመደብ እየሠራ መኾኑን አስታወቀ።
Next article“በእልህ ግጭትን ከማባባስ ይልቅ ተወያይቶ ችግሮችን መፍታት ዘላቂ መፍትሔን ያመጣል” የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት