የጎንደር ከተማ አሥተዳደር የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ በመመደብ እየሠራ መኾኑን አስታወቀ።

21

ጎንደር: የካቲት 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ኅብረት ሥራ ማኅበራት ማደራጃ ተጠሪ ጽሕፈት ቤት የግማሽ ዓመት አፈጻጸም እና የቀጣይ አቅጣጫዎችን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ገምግሟል።

በመድረኩ የተገኙት የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ደብሬ የኋላ የከተማዋ ኅብረት ሥራ ማኅበራት በከተማው ያለውን የኑሮ ውድነት በማረጋጋት በኩል ሰፊ ሥራ እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የኅብረት ሥራ ማኅበራቱ በስሩ ብዛት ያላቸው አባላት ያሉት እና የአካባቢው ማኅበረሰብ ተጠቃሚ እንዲኾን በትጋት እየሠራ ይገኛልም ብለዋል።የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ኅብረት ሥራ ማኅበራት በስድስት ወራት የተፈጠረውን የኑሮ ውድነት ለማቃለል በስፋት ሲሠራ መቆየቱን የተጠሪ ጽሕፈት ቤቱ ኀላፊ ሲሳይ አዳነ ገልጸዋል፡፡

ኀላፊው ሸማች ማኅበራት የሐሙስ ገበያን በማዘጋጀት ለማኅበረሰቡ በቅናሽ ዋጋ ሸቀጦችን የማቅረብ፣ ከከተማ አሥተዳደሩ በተበጀተ 20 ሚሊዮን ብር ጤፍ እና ሌሎች መሠረታዊ ፍላጎቶች እንዲቀርቡ መደረጉንም ገልጸዋል።

ኅብረት ሥራ ማኅበሩ ባለፉት ስድስት ወራት ከ90 በላይ የመኖሪያ ቤት ማኅበራትን የማደራጀት ሥራ ሠርቷልም ብለዋል።ተጠሪ ጽሕፈት ቤቱ ምንም እንኳን የተሻሉ ሥራዎችን ሲሠራ ቢቆይም የካፒታል እጥረት ፈተና እንደኾነበትም አቶ ሲሳይ ገልጸዋል።

በከተማዋ የሚገኙ የሸማች ኅብረት ሥራ ማኅበራትን በማጠናከር እና እየገጠማቸው የሚገኘውን የካፒታል እጥረት ለመፍታት ከተማ አሥተዳደሩ እየሠራ እንደሚገኝ ምክትል ከንቲባ ደብሬ የኋላ ገልጸዋል።

በሌላ በኩል ከፍተኛ የኾነ የመኖሪያ ቤት ፍላጎት እንዳለ ያነሱት ምክትል ከንቲባዋ የማኅበረሰቡን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመቅረፍም ባለው የመሬት ሃብት ልክ እንደሚሰጥም አንስተዋል።

በኅብረት ሥራ ማኅበሩ የገንዘብ እና ቁጠባ ማኅበራት፣ ሁለገብ የገበሬዎች ኅብረት ሥራ ማኅበራት፣ በማድለብ የተደራጁ እና ሌሎቹም ማኅበራት ተጠቃሚ መኾናቸውን ነግረውናል።

በማኅበራቱ ውስጥ የሚገኙ አባላት የኑሮ ሁኔታቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ ስለመምጣቱ ጠቅሰው ማኅበራቱ ከራሳቸው አልፈው ለጎንደር እና አካባቢው ማኅበረሰብ ግልጋሎት እየሰጡ እንደሚገኙ ተጠቁሟል።

ዘጋቢ፡- ደስታ ካሳ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየሴቶችን ጥቃት በመከላከል ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ ሁሉም ማኅበረሰብ በኀላፊነት ስሜት እንዲሠራ ጥሪ ቀረበ።
Next articleየላሊበላ-ሙጃ – ቆቦ የኮንክሪት አስፖልት መንገድ ሥራ በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ ድጋፍ እና ክትትል እየተደረገ መኾኑን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአካባቢው ተወካይ ገለጹ፡፡