
ጎንደር: የካቲት 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በጎንደር ከተማ አሥተዳደር ሴቶች ሕጻናትና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ አዘጋጅነት የጎንደር ከተማ አማራ ሴቶች ማኅበር 7ኛ መደበኛ ጉባኤ ተካሂዷል።
የጉባኤው ተሳታፊዎች በክፍለ ከተሞች በሚያካሂዱት ወርሐዊ ውይይት ስለ ትምህርት፣ ሰላም፣ ጤና እና ሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ እንደሚመክሩ ገልጸዋል፡፡ የሴቶችን ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ እና ብድርን ከማመቻቸት አኳያ ጉድለቶች አሉ ብለዋል።
የጎንደር ከተማ አማራ ሴቶች ማኅበር ምክትል ሠብሣቢ መሠረት አዱኛ ማኅበሩ የሴቶችን የማኅበራዊ፣ የኢኮኖሚያዊ እና የፖለቲካዊ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ለማስቻል እየተሠራ ስለመኾኑ አስረድተዋል።
ሴቶች የኤች አይ ቪ ኤድስ፣ የማህፀን ጫፍ ካንሰር እና ሌሎችም የጤና እክሎች እንዳይገጥሟቸው ግንዛቤን በመፍጠር ጤናማ ቤተሰብን ለመፍጠር እየተሠራ መኾኑን አንስተዋል።
በ2006 ዓ.ም እና በ2007 ዓ.ም ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመተባበር ከ600 በላይ ለኾኑ ሴቶች ተዘዋዋሪ ብድር ከ8 ሚሊዮን በላይ የተሰጠ መኾኑን ያነሱት የማኅበሩ ምክትል ሠብሣቢ በሚፈለገው ልክ ብድሩ ተመላሽ ባለመኾኑ ለሌሎች ተደራሽ ማድረግ አለመቻሉን ጠቅሰዋል፡፡ ይህንንም ችግር ለመቅረፍ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እንደሚሠሩ ገልጸዋል።
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ሴቶች ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ ውብአካል ቢራራ ማኅበሩ በከተማዋ ሴቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ እየሠራ ቢኾንም በተገቢው ልክ ግንዛቤ ፈጥሮ የሴቶችን ጥቃት መከላከል እና ተጠቀሚ ማድረግ ላይ በበቂ አለመሠራቱን አንስተዋል፡፡ የሴቶችን ጥቃት መከላከል ብሎም ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ ሁሉም ማኅበረሰብ በኅላፊነት ስሜት እንዲሠራም ጥሪ ቀርቧል።
ዘጋቢ፡- ቃልኪዳን ኃይሌ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!