ሴቶች በሰላም ግንባታ ዘርፍ ያላቸውን እምቅ አቅም እንዲጠቀሙ ጥሪ ቀረበ።

41

ደብረ ብርሃን: የካቲት 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ) 113ኛው ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ48ኛ ጊዜ፣ በክልል እና በከተማ አሥተዳደር ደረጃ ደግሞ ለ29ኛ ጊዜ “ሴቶችን እናብቃ ልማት እና ሰላም እናረጋግጥ” በሚል መሪ መልእክት በደብረ ብርሃን ከተማ ተከብሯል።

የከተማ አሥተዳደሩ ሴቶች ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ በለጥሽ ግርማ እንዳሉት ሴቶች በማኅበራዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊ እና ፖለቲካዊ ዘርፎች ላይ የነቃ ተሳትፎ አድርገው ተጠቃሚነታቸው እንዲረጋገጥ በትኩረት ተሠርቷል።

መንግሥት እና መንግሥታዊ ካልኾኑ ድርጅቶች ጋር በመኾንም ይህንኑ የሴቶች ተሳትፎ ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማሳደግ እየሠሩ እንደኾነ ነው የተናገሩት። የከተማ አሥተዳደሩ ምክትል ከንቲባ ወርቃለማሁ ኮስትሬ ሴቶች ለዘመናት ፍትሕ ተነፍጓቸው የቆዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች መኾናቸውን ጠቅሰዋል። ይህም በሁሉም ዘርፎች ሀገራዊ እድገትን ወደ ኋላ የጎተተ ስለመኾኑ ነው የተናገሩት።

አሁን ላይ ሴቶች በውስጣቸው የእንችላለን ስሜት አድሮባቸው በሁሉም ዘርፎች ተሳታፊ እንዲኾኑ የተጀማመሩ ሥራዎች ተጨባጭ ለውጥ አምጥተዋልም ብለዋል። በከተማ አሥተዳደሩ የሴቶች ፖለቲካዊ ተሳትፎ 30 በመቶ መድረሱንም በማሳያነት ጠቅሰዋል።

የበለጠ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ መንግሥት የድርሻውን ይወጣል ያሉት አቶ ወርቃለማሁ መቻላቸውን በተግባር ማሳየት ግን የሴቶች ድርሻ መኾን እንደሚገባው አስገንዝበዋል።
በከተማ አሥተዳደሩ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኀላፊ ቅመም አሽኔ ኢትዮጵያ እንደ እቴጌ ጣይቱ ብጡል ዓይነት ጀግና ሴቶች የተገኙባት ድንቅ ምድር ነች ብለዋል።

ኀላፊዋ ሴቶች በሰላም ግንባታ ዘርፍ ያላቸውን እምቅ አቅም ሊጠቀሙ ይገባል ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።የበዓሉ ተሳታፊዎች በሰጡት ሃሳብ አሁን ላይ የሴቶች ተሳትፎ ማደግ ትልቅ ስኬት ተደርጎ ሊወሰድ ይገባል ብለዋል። ይሁን እንጂ ከሚፈለገው አንጻር በቂ ባለመኾኑ የሚመለከተው አካል ሁሉ ትኩረት እንዲሰጠው ጠይቀዋል።

ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበማዕከላዊ ጎንደር ዞን በጠገዴ ወረዳ የሰላም ጥሪውን የተቀበሉ ታጣቂዎች ወደ ሰላማዊ ሕይወት ተመለሱ።
Next articleየሴቶችን ጥቃት በመከላከል ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ ሁሉም ማኅበረሰብ በኀላፊነት ስሜት እንዲሠራ ጥሪ ቀረበ።