የሴቶችን ተሳትፎ በኹሉም ዘርፍ ውጤታማ ለማድረግ እየሠራ መኾኑን የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ገለጸ፡፡

18

ሰቆጣ: የካቲት 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ) “ሴቶችን እናብቃ፤ ልማት እና ሰላምን እናረጋግጥ” በሚል መሪ መልእክት በሰቆጣ ከተማ ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ተከብሯል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ113ኛ ጊዜ፣ በኢትዮጵያ ለ48ኛ ጊዜ እና በአማራ ክልል ለ29ኛ ጊዜ የሚከበረው” ማርች ኤይት” የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎ እንደሚያሳድገው ተሳታፊዎቹ ተናግረዋል።

የበዓሉ ተሳታፊ ወይዘሮ ካባ ሲሳይ የሴቶች ቀን መከበሩ “እኛ ሴቶች ያሉብንን ችግሮች ተወያይተን በመፍታት በፖለቲካው፣ በኢኮኖሚው እና በማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ያለንን ተሳትፎ እንድናሳድግ የሚያግዝ ነው” ብለዋል።

ሴቶች በአመራር ብስለታቸው የሚታወቁ ናቸው ያሉት ሌላዋ ተሳታፊ ወይዘሮ አድና ባየ “የሴቶችን ቀን ስናከብር ለዛሬዋ ቀን ዋጋ የከፈሉ እህቶቻችንን ማሰብ ያስፈልጋል” ነው ያሉት።
የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ሴቶች ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ ትቨርህ ታደሰ የዘንድሮው የሴቶች ቀን ታሪካዊው የዓድዋ የድል ቀን መታሰቢያ ሙዚየም በተገነባበት ማግስት መከበሩ ልዩ እንደሚያደርገው አስረድተዋል፡፡

በክልሉ ብሎም በዋግኽምራ ያለውን አንጻራዊ ሰላም ለማስጠበቅ ሴቶች ኀላፊነታቸው ከፍ ያለ ስለመኾኑም ነው የተናገሩት፡፡
የሴቶች ቀን በዓመት አንድ ቀን ብቻ ታስቦ የሚውል አይደለም ብለዋል፡፡ ኀላፊዋ የሴቶችን ተሳትፎ በኹሉም ዘርፍ ግንባር ቀደም እና በሥራቸውም ውጤታማ እንዲኾኑ እየተሠራ ስለመኾኑም አስገንዝበዋል።

ዘጋቢ፡- ደጀን ታምሩ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየደብረ ብርሃን ከተማ የፍሳሽ ቆሻሻ ማጣሪያ ፕሮጀክት የግንባታ ሥራ ተጀመረ።
Next articleበኩር ጋዜጣ የካቲት 25/2016 ዓ.ም ዕትም