
ባሕር ዳር: የካቲት 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ፍልሰትን እና ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት ተቋማት እንዲደግፉ የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጥሪ አቅርቧል።
ሚኒስቴሩ ባለፉት ስድስት ወራት ፍልሰትን እና ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል በግንዛቤ ፈጠራ ዙሪያ የተከናወኑ ተግባራትን ተመልክቷል፡፡
የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ድኤታ ሁሪያ ዓሊ በዚህ ወቅት ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ዜጎች በየጊዜው በሕገ ወጥ መንገድ ከሀገር ሲወጡ በድንበር ጠባቂዎች እና ሌሎች የተደራጁ አካላት እጅ እየወደቁ ከፍተኛ ለኾነ የጤና፣ የሥነ ልቦና፣ የአካል ጉዳት እና ወሲባዊ ጥቃት እንደሚደርስባቸው ተናግረዋል።
ይህንን ለመከላከል መንግሥት በትኩረት እየሠራ ነው ብለዋል፡፡ ሚኒስትር ድኤታዋ መደበኛ ያልኾነ ፍልሰትን ለመከላከል የተለያዩ ተቋማትን ያቀፈ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ ተሠርቷል፡፡
ወይዘሮ ሁሪያ ዓሊ የሥራ ቡድን በአዋጅ ተቋቁሞ ወደ ሥራ መግባቱን እና ባለፉት ስድስት ወራትም የተለያዩ ተግባራት በቅንጅት ሲያከናወን መቆየቱን አብራርተዋል።
የጥምረቱ አባል ተቋማት በቀጣይ ፍልሰትን እና ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል እና የተጎጂዎችን ሰብዓዊ መብት ለማስከበር በሚደረገው ሀገራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ የተቀናጀ አገልግሎት እንዲሰጡ እና የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱም ጥሪ አቅርበዋል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ መደበኛ ያልኾነ ፍልሰት የወንጀል ድርጊት መኾኑን እና አስከፊነቱን ለኅብረተሰቡ ለማስገንዘብ፣ ተጎጂ የኾኑ ተመላሽ ዜጎችን ማኅበራዊ እና ሥነ ልቦናዊ ድጋፍ ለመሥጠት እንዲሁም ፍልሰትን የተመለከተ ሀገራዊ መረጃ ለማደራጀት እየሠራ መኾኑን ኢቢሲ ዘግቧል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!