
ደብረ ብርሃን: የካቲት 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ ታምርት የኢንዱስትሪ ፎረም ምክክር በደብረ ብርሃን ከተማ እየተካሄደ ነው። በፎረሙ መክፈቻ ላይ የተገኙት የከተማ አሥተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት እና የኢንዱስትሪዎችን ምርታማነት ለማሳደግ ታሳቢ ተደርጎ የተዘጋጀ መድረክ ስለመኾኑ ጠቁመዋል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኀላፊ እንድሪስ አብዱ በበኩላቸው እየተካሄደ ያለው የኢትዮጵያ ታምርት ፎረም በክልሉ የበጀት ዓመቱ የማስጀመሪያ መርሐ ግብር ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በክልሉ 255 የማኑፋክቸሪንግ ኢንደስትሪዎች ወደ ሥራ መግባታቸውንም ገልጸዋል።በዘርፉ የምርት እና ምርታማነት እንዲሁም የቅንጅታዊ አሠራሮች ጉድለት እንደነበር በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተማ ልማት ዘርፍ አስተባባሪና የከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አሕመዲን መሀመድ (ዶ.ር) ተናግረዋል።
ከመንግሥት በኩል ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር፣ አልሚ ባለሃብቶች ፈጥነው ወደ ምርት እንዲገቡ ማድረግ እና ኢንደስትሪዎችን የሚንከባከብ ማኅበረሰብ መፍጠር እንደሚገባም አብራርተዋል።
በመድረኩ የተለያዩ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች፣ የመሠረተ ልማት ተቋማት ፣ አልሚ ባለሃብቶች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳታፊዎች ናቸው።
ዘጋቢ :- በላይ ተስፋዬ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!