
ወልድያ: የካቲት 25/2016 ዓ.ም(አሚኮ) ዩኒቨርሲቲው የሰሜን ወሎ እና የዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር የትራንስፖርት አገልግሎት ላይ ያተኮረ ጥናት አድርጓል።
ከሁለቱ ዞኖች ከተውጣጡ የባለድርሻ አካላት ጋርም በጥናት ግኝቱ ላይ ምክክር አድርጓል።
የሰሜን ወሎ ዞን መንገድ ትራንስፖርት መምሪያ ኀላፊ ባንቴ ምሥጋናው አሁን ላይ የወልድያ መናኽሪያን ጨምሮ በየከተሞቹ ያለው የአውቶብስ መናኽሪያ አገልግሎት በተገቢው መንገድ ባለመመራቱ የትራንስፖርት አገልግሎቱን ፈታኝ አድርጎታል ብለዋል።
ታሪፍ እና መስመር የሚወስኑት ደላሎች ኾነዋል፤ በዚህም መንገደኛን በማንገላታት ተገቢ አገልግሎት አንዳያገኝ እንቅፋት ኾኗል ነው ያሉት። ተገልጋዩ ማኅበረሰብም የትራንስፖርት ደምብ አስከባሪዎችን እየተባበረ እንዳልኾነ መምሪያ ኀላፊው ገልጸዋል።
ዘመናዊ መናኽሪያ አለመኖር፣ በቴክኖሎጂ የታገዘ የትራንስፖርት አደረጃጀት አለመኖር እና የባለድርሻ አካላት የግንዛቤ እጥረት ለችግሩ በምክንያትነት የተጠቀሱ ናቸው። ይህንንም ወልድያ ዩኒቨርሲቲ በጥናቱ አረጋግጧል።
የወልድያ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ሽግግር እና የማኅበርሰብ አገልግሎት ዳይሬክተር አማረ ቢኾን (ዶ•ር) ዩኒቨርሲቲው የትራንስፖርት ዘርፉን ለማዘመን ከባለድርሻዎች ጋር በጥምረት እንደሚሠራ ነው የገለጹት።
በእለቱ የተፈራረሙት የመግባቢያ ስምምነትም ከግንባታ ሥራ ውጭ ያሉ የሥልጠና፣ የቴክኖሎጂ ማበልጸግ፣ የዲዛይን እና መሰል ሙያዊ ድጋፎችን ለማድረግ የሚያስችል መኾኑን ገልጸዋል።
ዘጋቢ፡- ካሳሁን ኃይለሚካኤል
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!