
አዲስ አበባ: የካቲት 25/2016 ዓ.ም(አሚኮ)የኢትዮጵያ ኅብረት ሥራ ማኅበራት ለኢትዮጵያ ብልጽግና በሚል መሪ መልእክት የኅብረት ሥራ ማኅበራት ኮሚሽን ከብልጽግና ፓርቲ አመራሮች ጋር በኮሚሽኑ ሪፎርም ዙሪያ ውይይት እያካሔደ ነው።
በውይይቱ መክፈቻ ላይ የተገኙት የፌዴራል የኅብረት ሥራ ማኅበራት ኮሚሽን ኮሚሽነር ጌታቸው መለሰ (ዶ.ር) የኅብረት ሥራ ማኅበራት ለኢኮኖሚ ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማድረግ ከድህነት መውጫ መሰላል ናቸው ብለዋል።
በሀገሪቱ የሚገኙ 110 ሺህ መሠረታዊ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ለ4 ሚሊዮን ዜጎች የሥራ እድል መፍጠር የቻሉ ሲኾን 49 ቢሊዮን ብር ካፒታል ማፍራት ስለመቻላቸውም ተናግረዋል።
ይሁንና የማኅበራቱ የቴክኖሎጂ፣ የአመለካከት፣ የፋይናንስ፣ የአደረጃጀት እና የሕግ ማዕቀፍ ችግር ለማኅበራቱ ፈታኝ ኾነውባቸዋል ብለዋል። ችግሩን ለመቅረፍ የጥናት ቡድን ተቋቁሞ ተሠርቷልም ነው የተባለው።
በመኾኑም 63 ዓመታት ያስቆጠረው የኅብረት ሥራ ተቋም መሠረታዊ ለውጥ እንዲያመጣ እና የምጣኔ ሃብት አንቀሳቃሽ አንዲኾን በማሰብ ኮሚሽኑ የምክከር መድረክ እያካሔደ ስለመኾኑ ነው የተገለጸው።
ዘጋቢ፡- አንዱዓለም መናን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!