
ባሕር ዳር: የካቲት 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የጤና ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያሳየው በዓለም ላይ ከ17 ሚሊዮን በላይ ሰዎች 70 ዓመት ሳይሞላቸው ተላላፊ ባልኾኑ በሽታዎች ህይወታቸውን ያጣሉ።
በማደግ ላይ በሚገኙ ሀገራት ደግሞ ይበልጥ ስጋት እየኾኑ ይገኛል። ከእነዚህ በሽታዎች ውስጥ ደግሞ የማህጸን በር ካንሰር አንዱ ነው። በዓለም ላይ በዚህ በሽታ ከሚሞቱት ሰዎች 90 በመቶ የሚኾኑት ከሰሀራ በታች በሚገኙ ሀገሮች እንደኾነ ነው የተገለጸው።
በሽታው በኢትዮጵያም ከጡት ካንሰር ቀጥሎ በገዳይነቱ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። በዓመት እስከ 7 ሺህ እናቶች በዚህ ካንሰር ይያዛሉ፤ እስከ 5 ሺህ እናቶች ደግሞ ህይወታቸው ያልፋል።
የግብረ ስጋ ግንኙነት ከጀመሩ ሴቶች ከአምስቱ አራቱ በህይወት ዘመናቸው ለማህጸን በር ካንሰር ተጋላጭ ይኾናሉ። በለጋ እድሜ ( ከ18 ዓመት በታች ) ፆታዊ ግንኙነት መጀመር እና ልቅ የኾነ የግብረ ስጋ ግንኙነት ካንሰሩን ለሚያመጣው ቫይረስ ይበልጥ ተጋላጭ ያደርጋል ተብሏል።
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ የእናቶች እና ሕጻናት ጤና ከፍተኛ አማካሪ እና የማህፀን እና ጽንስ ህክምና ስፔሻሊስት የኾኑት ፈቃዴ ጌታቸው (ዶ.ር) እንዳሉት የማህጸን በር ካንሰር በአብዛኛው በቫይረስ የሚመጣ በሽታ ነው።
80 በመቶ የሚኾኑት ፆታዊ ግንኙነት የሚያደርጉ ሴቶች በህይወት ዘመናቸው በቫይረሱ የመያዝ እድላቸው ከፍተኛ እንደኾነ ገልጸዋል። ከእነዚህ ውስጥ 90 በመቶ የሚኾኑት በተፈጥሮ ባላቸው የመከላከል አቅም ለማህፀን በር ካንሰር አጋላጭ የኾነው ቫይረስ ከሰውነታቸው የሚወገድ ሲኾን 10 በመቶው ግን በቅድመ ካንሰር እና ካንሰር ይያዛሉ።
ከ10 በመቶው ውስጥ አንድ በመቶ የሚኾኑት የማኅጸን በር ካንሰር እንደሚያሳዩ ነው የገለጹት። በተለይም ደግሞ እድሜያቸው ያልደረሱ ሴቶች በለጋ እድሜያቸው ፆታዊ ግንኙነት ሲጀምሩ ለቫይረሱ ይበልጥ ተጋላጭ መኾናቸው ተገልጿል። ከተለያዩ ሰዎች ጋር ግንኙነት መፈጸም፣ ሲጋራ ማጨስ እና የመሳሰሉ ምክንያቶች በማህፀን በር ካንሰር የመያዝ እድልን ከፍ የሚያደርጉ ምክንያቶች መኾናቸው ተቀምጧል።
ዶክተር ፈቃዴ እንዳሉት የዓለም ጤና ድርጅት የማህጸን በር ካንሰር በሽታን በ2030 (እ.አ.አ) የማኅበረሰብ ችግር እንዳይኾን ለማድረግ እየሠራ ይገኛል። ኢትዮጵያም እቅዱን ለማሳካት ከ2009 (እ.አ.አ) ጀምሮ የቅድመ ካንሰር ምርመራ እያደረገች ትገኛለች።
በአማራ ክልል በአምስት ዓመት ውስጥ 2 ሚሊዮን ለሚኾኑ እናቶቸ የቅድመ ካንሰር ምርመራ ለማድረግ ታቅዶ ወደ ሥራ ተገብቷል። እንዲሁም 90 በመቶ ለሚኾኑ ልጃገረዶች የማህጸን በር አምጭ የኾነውን ቫይረስ መከላከያ ክትባት መስጠት፣ ከ30 እስከ 49 የእድሜ ክልል ለሚገኙ 70 በመቶ ሴቶች የቅድመ ካንሰር ምርመራ መሥጠት፤ ቅድመ ካንሰር ከተገኘባቸው ውስጥ ደግሞ 90 በመቶ የሚኾኑት ሕክምና እንዲያገኙ ማድረግ ዓላማ ተደርጎ ነበር ወደ ተግባር የተገባው።
በክልሉ በሚገኙ 300 ጤና ተቋማት አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል። ይሁን እንጅ ባለፉት ሦስት ዓመታት ቅድመ ምርመራ የተደረገላቸው እናቶች ከ200 ሺህ እንደማይበልጡ ነው የተገለጸው። በ2016 የመጀመሪያው ግማሽ ዓመት ደግሞ ሁለት መቶ ሺህ ለሚጠጉ እናቶች የቅድመ ካንሰር ምርመራ ለማድረግ ታቅዶ ተደራሽ ማድረግ የተቻለው ግን ወደ 22 ሺህ ለሚኾኑት ብቻ ነው።
ባለፉት ዓመታት ተከስተው የነበሩት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ፣ የሰሜኑ ጦርነት እና አሁንም በክልሉ የተከሰተው የጸጥታ ችግር ለእቅዱ አለመሳካት በምክንያትነት ተቀምጠዋል። ከዚህ ባለፈ ለማኅበረሰቡ የተደረገው የግንዛቤ ፈጠራ ዝቅተኛ መኾን፣ ግንዛቤ የተፈጠረላቸውም ያለመቀበል፣ በሙሉ አቅም ወደ ሥራ አለመግባት ሌሎች ችግሮች ናቸው።
በቀጣይ በተለያዩ ሚዲያዎች እና በየደረጃው የሚገኙ የተቋሙን ባለሙያዎች በማሳተፍ ማኅበረሰቡን የማስገንዘብ ሥራ እንደሚሠራ አንስተዋል። በዚህ ወቅትም ቫይረሱን ለመከላከል የሚያስችል ክትባት ለልጃገረዶች እየተሠጠ እንደሚገኝ ገልጸዋል። ክትባቱ ደኅንነቱ የተጠበቀ እና በበርካታ ሀገሮች የሚሰጥ ክትባት እንደኾነ ጠቅሰዋል።
በሁሉም ጤና ጣብያዎች እና ሆስፒታሎች በመሄድ ምርመራ ማድረግ እንደሚገባም አሳስበዋል። ተማሪዎች፣ መምህራን፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች ለጤና ባለሙያዎች አጋዥ እንዲኾኑ ጠይቀዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!