
ደሴ: የካቲት 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ተአማኒ እና ተጨባጭ መረጃን ለማቅረብ ወሳኝ ኩነትን በተገቢው መንገድ መፈጸም አስፈላጊ እንደኾነ የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ አገልግሎት አስታውቋል።
በአማራ ክልል ወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ አገልግሎት ለመዝጋቢ አካላት እና ለሚመለከታቸው የጤና ባለሙያዎች ስለአንድ ማዕከል አገልግሎት የተዘጋጀ የትውውቅ መድረክ በኮምቦልቻ ከተማ ተካሂዷል።
በምክክር መድረኩ በተቋሙ በባለፉት ስድስት ወራት የተሠሩ ሥራዎች ተገምግመዋል። በዕቅድ አፈጻጸም ላይ ያጋጠሙ ችግሮች እና የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዋች ዙሪያም ውይይት ተደርጓል።
እንደ ክልል ያለውን የመረጃ አያያዝ በማዘመን የወሳኝ ኩነት ምዝገባን በተደራጀ እና በተጠና መልኩ ለመያዝ የምክክር መድረኩ ልምድ የቀሰሙበት እንደኾነ በምክክር መድረኩ የተገኙ ተሳታፊዎች ተናግረዋል።
ለክልሉ ብሎም ለሀገሪቱ ተአማኒ እና ተጨባጭ መረጃን ለማቅረብ የወሳኝ ኩነትን በተገቢው መንገድ መፈጸም አስፈላጊ እንደኾነ በአማራ ክልል ወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ አገልግሎት ኀላፊ መዓዛ በዛብህ ተናግረዋል።
ኀላፊዋ ቴክኖሎጅን በመጠቀም የአንድ ማዕከል ምዝገባ ማበልፀግ የትኩረት አቅጣጫ እንደኾነም ነው ያስገነዘቡት።
በቀጣይ የአንድ ማዕከል ምዝገባን በማጠናከር እና ቴክኖሎጂን በመጠቀም አገልግሎትን ማዘመን የትኩረት አቅጣጫዎች እንደኾኑ በውይይት መድረኩ ተነስቷል።
ዘጋቢ፦ ደምስ አረጋ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!