
ደሴ: የካቲት 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ በግማሽ ዓመት የተከናወኑ ሥራዎች እና የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል።
በክልሉ የተፈጠረው የሰላም እጦት ተማሪዎች ትምህርታቸው ላይ እክል እንደፈጠረ በግምገማ መድረኩ ላይ ተንስቷል። የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አልይ ተፈራ በዞኑ ባለው አንፃራዊ ሰላም መልካም የመማር ማስተማር ሂደት ላይ እንዳለ ገልጸዋል። ክልል አቀፍ እና ብሔራዊ ፈተና የሚወስዱ ተማሪዎች ጥሩ ውጤት እንዲያስመዘግቡ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል። ከክልሉ ወቅታዊ ሁኔታ ጋር ተያይዞ በዞኑ የሚገኙ 26 ትምህርት ቤቶች መማር ማስተማር አለመጀመራቸውን የተናገሩት የሰሜን ወሎ ትምህርት መምሪያ ኃላፊ ሰጠ ታደሰ በተማሪዎች እና በማኅበረሰቡ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እያሳደረ ነው ብለዋል።
የደቡብ ወሎ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ የሆኑት አቶ ዓለምነው አበራ በበኩላቸው በዞኑ እስካሁን ድረስ ምንም አይነት የመማር ማስተማር ሂደት ያልጀመሩ ትምህርት ቤቶች እንዳሉ ጠቁመው ወደ ሰላም በተመለሱ አካባቢዎች የመማሪያ ግብዓቶችን የማሟላት ሥራ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።በጸጥታ ችግር ጋር ተያይዞ ከ2 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ውጭ መሆናቸውን እና ከ3ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶች ማስተማር ማቆማቸውን የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሙሉነሽ ደሴ ለአሚኮ ተናግረዋል።
በሰሜኑ ጦርነት ጉዳት የደረሰባቸውን ትምህርት ቤቶች በአዲስ መልክ በመሥራት እኳያ ከመንግሥት እና ከአጋር ድርጅቶች ጋር በጋራ እየተሠራ ነው ሲሉ ዶክተር ሙሉነሽ ገልጸዋል። በቀጣይ የመማር ማስተማር ሂደቱን ለማሳለጥ ሰላም አስፈላጊ በመሆኑ ለዚህም ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እምደሚገባ አሳስበዋል።
ዘጋቢ:- ሰልሀዲን ሰይድ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!