
ደብረ ብርሃን: የካቲት 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ሰሜን ሽዋ ዞን ደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር በተለያየ የምርት ዓይነቶች የተሰማሩ አራት አምራች ኢንዱስትሪዎች ይመረቃሉ። በምረቃ መርሐ ገብሩ ላይ የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ፣ ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተማ ልማት ዘርፍ አስተባባሪ እና የከተሞች እና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አህመዲን መሀመድ (ዶ.ር)፣ የኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኀላፊ እንድሪስ አብዱን ጨምሮ ሌሎች የፌደራል፣ የክልል፣ የዞን እና የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
ዛሬ የሚመረቁት ኢንዱስትሪዎች ዛሙ ኀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ ኤም ዲ ኤፍ ማምረቻ፣ ጅንሹ ኢትዬጵያ ቴክስታይል ቴክኖሎጂ እና ሂንዲ ፕላስቲክ ማኑፍክቸሪንግ እና ሊሃም ትሬዲንግ የምግብ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ናቸው።
በከተማ እና መሠረተ ልማት፣ ህንጻ ሹም እንዲሁም በከተማ ካዳስተር አሰራር የዲጂታል የአገልግሎት አሰጣጡን ለማዘመን የተሠሩ ሥራዎችን ቅኝት ይደረጋል ተብሏል። በከተማው 39 ሺህ ፋይሎች ወደ ዲጂታል የፋይል አደረጃጀት ተቀይረዋል። የሴኩሪት ካሜራም በከተማ አስተዳደሩ የአገልግሎት አሰጣጡ ሂደት ላይ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል ተብሏል።
ዘጋቢ፦ በላይ ተስፋየ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!