
ባሕር ዳር: የካቲት 23/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ብልሆች ችግሮቻቸውን በምክክር ይፈታሉ። በምክክር ደም ያደርቃሉ። በምክክር የዜጎቻቸውን ሞት ያስቀራሉ። ያልታረቁ ሀሳቦችን እያስታረቁ፣ ጦር መማዘዝን በመተቃቀፍ እየቀየሩ የሀገራቸውን አንድነት ያጠናክራሉ። ሀገራቸውንም በሥልጣኔ እና በልማት ከፍ ያደርጋሉ።
ችግሮቻቸውን በጦርነት ለመፍታት የተነሱ ሀገራት የሀገራቸውን ምጣኔ ሀብት አድቅቀዋል። ዜጎቻቸውን ተነጥቀዋል። በሂደትም ሀገር አልባ ኾነዋል። በማለዳው ያልተገታ ግጭት እየቆዬ ሄዶ ሀገርን እስከማሳጣት ይደርሳልና። ሀገር በችግር ውስጥ ስትገባ፣ በጦርነት ስትወጠር ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር ብሔራዊ ምክክር ይደረጋል።
ለብሔራዊ ችግሮቻቸው ብሔራዊ ምክክሩን በሚገባ የተጠቀሙበት ችግሮቻቸውን ፈትተው የጋራ እቅድ ያቅዳሉ፣ የጋራ ራዕይ ይሰንቃሉ፣ የጋራ ሀገር ይገነባሉ። ለብሔራዊ ችግሮቻቸው ብሔራዊ ምክክርን የገፉ ደግሞ በችግር ውስጥ እንዲኖሩ ይገደዳሉ። ኢትዮጵያ ለዓመታት ተዘርተው፣ ለዓመታት አፍርተው የሰላም፣ የአንድነት፣ የፍቅር፣ የመቻቻል፣ የመተሳሰብ እና በጋራ የማደግ ችግሮቿን ለመቅረፍ ሀጋረዊ ምክክር ለማድረግ ጉዞ ከጀመረች ውላ አድራለች።
ሀገራዊ ምክክር የሚደረገው ሀገር በችግር ውስጥ በወደቀችበት ጊዜ ነውና በኢትዮጵያ ሊደረግ የታሰበው ምክክርም የኢትዮጵያን ችግሮች ይፈታል ተብሎ ታላቅ ተስፋ ተጥሎበታል። በየአካባቢው ያሉ እና ያልታረቁ ጥያቄዎች፣ ለግጭት ምክንያት የኾኑ ፍላጎቶች በሀገራዊ ምክክር ውስጥ ታርቀው እና የጋራ ኾነው ኢትዮጵያ ሰላሟ ይመለሳል፣ ችግሮቿም ይፈታሉ ተብሎ ተስፋ ተደርጓል። ታዲያ ይህ ከጭንቅ ይገላግላል ተብሎ የተሰነቀው ተስፋ እውን ይኾን ዘንድ በርካታ ሂደቶችን ማለፍ እና ሂደቱን መደገፍ ግድ ይላል። በመንገዱ ያልተግባቡ በመድረሻው አይግባቡምና።
በደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር ጣዕሙ ዓለሙ እንደ ሀገር ብሔራዊ የምክክር ኮሚሽን መቋቋም በራሱ ታላቅ እርምጃ ነው ይላሉ። ኢትዮጵያ በብዙ ችግሮች ውስጥ ያለች ሀገር ናት የሚሉት መምህሩ በአንድ በኩል ያላባራ ደም አፋሳሽ ግጭት፣ በሌላ በኩል ቆዬት ያሉ እና መስተካከል የሚገባቸው ችግሮች አሉባት ነው የሚሉት። በበርካታ ችግር ውስጥ ላለች ሀገር ደግሞ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን መቋቋም እንደ አንድ በጎ ነገር መወሰድ አለበት ይላሉ። ጥሩ ውጤት የሚገኘው ጅምሩ ያማረ ሲኾን ነውና። የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በርካታ ተልዕኮ ተሰጥቶት፣ በርካታ ተስፋ ተጥሎበት የተቋቋመ መኾኑን የሚያነሱት መምህሩ የተባለለትን ዓላማ የሚያሳካ ከኾነ የሀገሪቱን ችግር ማስተካከል ይችላል ይላሉ። ነገር ግን ይላሉ ምሁሩ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን መመሥረቱ ብቻ በቂ አይደለም፣ አካሄዱ እና አተገባበሩ የተስተካከለ መኾን መቻል አለበት። አካሄዱ የተሳሳተ ከኾነ ፍፃሜው እና ውጤቱም የተሳሳተ ይኾናልና።
ተቋሙ ማድረግ የሚገባውን ማድረግ ከቻለ የኢትዮጵያን መሠረታዊ ችግሮች ማስተካከል የሚችል አቅም አለው ነው ያሉት። የምክክር ኮሚሽኑ ስኬታማ እንዲኾን በርካታ ሂደቶች ማለፍ ይጠበቅበታል፣ በቂ የኾነ ዝግጅት ማድረግ፣ አጀንዳ መምረጥ፣ በታለመለት ሂደት ውስጥ ማለፍ አለበት ነው ያሉት። የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑን መንግሥት፣ ቡድኖች፣ ግለሰብ፣ የሃይማኖት ተቋማት እና ሌሎች ጫና ሊያሳድሩበት ይችላሉ የሚሉት ምሁሩ ይሄን ሁሉ ተቋቁሞ ማለፍ ለውጤታማነቱ ታላቅ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል። የዘር፣ የሃይማኖት ፣ የቋንቋ፣ የመደብ እና ሌሎች ልዩነቶችን በማቻቻል አካታችነትን በሚገባ መወጣት ሌላኛው ለውጤታማነቱ መሠረት ነው።
የተለያየ የታሪክ አረዳድ ያላቸውን አካላት፣ በቁጥር የበዙትን እና ያነሱትን በአንድነት በማየት በልካቸው ማካተት የተገባ ነው ይላሉ ምሁሩ። የተለያየ ፍላጎት ያላቸው ቡድኖች አሉ፣ እነርሱን ማሳተፍ እና ማካተት ለውጤታማነቱ መሠረታዊ ጉዳይ ነው። የተሳታፊዎቹ ቅንነትም ለውጤታማነቱ አስተዋጽኦው የጎላ ነው ብለዋል።
በዓለም ላይ ለሁለት ዓላማ ምክክር ይደረጋል፣ አንደኛው ለማሸነፍ፣ ሁለተኛው ደግሞ ለመማር የሚደረግ ምክክር ነው የሚሉት ምሁሩ በምክክር ኮሚሽኑ አሸናፊ ተሸናፊ የሚባል ላይኖር ይችላል፣ የአንደኛው ፍላጎት በሌላኛው ጭኖ ማለፍ ሳይኾን ፍላጎትን በአንድ አድርጎ የመሄድ ሂደት ነው ይላሉ። ፍላጎትን አስታርቆ በአንድ ለመሄድ አካታችነቱ ላይ ልዩ ትኩረት ሊሰጥበት ይገባል ነው ያሉት። የመንግሥት ጣልቃ ገብነት እየላላ እና የምክክር ኮሚሽኑ ራሱን ችሎ እየቆመ በሄደ ቁጥር የምክክር ኮሚሽኑ ውጤታማነት እየገዘፈ እንደሚሄድም አንስተዋል። በምክክር ኮሚሽኑ መንግሥት ብቻ የለያቸው ተሳታፊዎች ከተገናኙ ውይይቱ የአንድ አካል ብቻ ይኾናልም ብለዋል። ለሀገራዊ ምክክር ውጤታማነት ገለልተኛ አካሄድ ያስፈልገዋል ነው ያሉት።
በዓለም ላይ ከተደረጉ የምክክር ሂደቶች ወደ ተግባር የገቡት 50 በመቶ ብቻ ናቸው ያሉት ምሁሩ ከምክክር በኋላ የመጣውን ውጤት አምኖ መቀበል ሌላ ችግር ነው ብለዋል። ምንም ይሁን ምን፣ የሕዝብ ድምጽ ነው፣ የሁላችንም ፍላጎት ነው ብሎ መቀበል ለውጤታማነቱ ሌላው መሠረታዊ ጉዳይ መኾኑንም አመላክተዋል። በምክክሩ የተገኘውን ውጤት አለመቀበል ድካሙን ባዶ ያደርገዋል ነው ያሉት።
ሀገራዊ የምክክር ሂደት ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው ድረስ በጥንቃቄ መመራት አለበትም ብለዋል። ሀገራዊ ምክክር ከመጀመሪያው ከተበላሸም አያምርም፣ ሄዶ ሄዶ ውጤቱን መቀበል ካልተቻለም አያምርም፣ የተሳካም ሳይኾን ይቀራል ነው ያሉት። በእያንዳንዱ ምዕራፍ መቻቻልን ሁላችንም አሸንፈናል ብሎ መቀበልን ይጠይቃልም ብለዋል።
በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ አይፈቱም ተብለው የሚነሱ ችግሮች ያሉ አይመስለኝም የሚሉት ምሁሩ ችግሮቹን በረጅም ጊዜ እና በአጭር ጊዜ መፍታት ይቻላል ነው ያሉት። የሀገርን ሉዓላዊነት ማስከበር እና ሰላምን ማስፈን በአጭር ጊዜ ውስጥ መፈታት ያለበት ጉዳይ መኾኑንም አመላክተዋል። በሀገራዊ ምክክር ኪሚሽን የሚረጋገጠው የአንድ አካል ወይም የአንድ ቡድን ፍላጎት ሳይኾን የሁሉም አሸናፊነት ነው የሚረጋገጠው ብለዋል። የኔ ብቻ የሚል አካሄድ ለሀገር እንደማይጠቅምም አንስተዋል።
የኔ ብቻ ካልኾነ የሚል አካሄድ የኢትዮጵያን ታሪክ እንደማይመጥንም አብራርተዋል። በማኅበረሰብ ውስጥ የበዙ ጥበቦች አሉ የሚሉት ምሁሩ የምንወድቀው ለጥበቦች እውቅና መስጠት ሳንችል ስንቀር ነው ይላሉ። ሁሉንም ማድመጥ እንጂ፣ ከሌሎች ላይ እንጫንብህ፣ እኔን ብቻ አድምጠኝ የሚል ካለ ወደ ኋላ እንሸራተታለን እንጂ ወደፊት መገስገስ አይቻለንም ነው ያሉት። የፖለቲካ ልሂቃን ዘመናዊ የተግባቦት አማራጮችን እየተጠቀሙ የራሳቸውን ሀሳብ ለመጫን እንደሚጥሩም አንስተዋል። ይህ አካሄድ ደግሞ ሀገራዊ ምክክርን ይጎደዋል፣ ውጤቱንም ፍሬ ቢስ ያደርገዋል ባይ ናቸው።
ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስፈላጊነት በጣም ጎልቶ የሚታየው ሀገር ባለመረጋጋት ውስጥ ስትኾን ነው የሚሉት ምሁሩ ያልተረጋጋ ሀገር ሲኖር ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ አሉታዊ ተፅዕኖ ይኖረዋል፣ ነገር ግን ችግሩን ሰብሮ የሚወጣ የምክክር ኮሚሽን ይጠበቃል ብለዋል። የታጠቁ ኀይሎችም ኾነ መንግሥት ወይም በተለያየ ጎራ የተሰለፉ አካላት ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽንን ከችግር መውጫ መንገድ አድርገው ሊመለከቱት ይገባል፣ በምክክር ኮሚሽኑ ላይ የጋራ አቋም ሊኖራቸው ግድ ይላል ነው ያሉት።
ደቡብ አፍሪካን ጨምሮ ሌሎች ሀገራት በበርካታ ትርምስ ውስጥ አልፈው ሀገራዊ ምክክር ማድረጋቸውን አንስተዋል። በችግር ውስጥ አልፈውም በምክክር ኮሚሽን ችግሮቻቸውን መፍታታቸውን ገልጸዋል። በርካታ ሀገራትም ሳይሳካላቸው መቅረታቸውን አንስተዋል። ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጦርነትን የማስቀረት ፣ ችግሮች በውይይት እንዲፈቱ የማድረግ ኀላፊነት አለበት ነው ያሉት።
ብሔራዊ የምክክር ኮሚሽን ውጤታማ እና ስኬታማ እንዲኾን ካስፈለገ መንግሥት ጣልቃ እንዳይገባ መጠንቀቅ አለበት ብለዋል። የምክክር ኮሚሽኑ የሚያስፈልጉትን ድጋፎች ሲለዩ እየደገፈ ጣልቃ እንዳይገባ ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባል ነው ያሉት። የመንግሥት የመጀመሪያው ድጋፍ እጁን እንዳያስገባ ማድረግ ነውም ብለዋል። በብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን የበላይ እና የበታች የሚባል ደረጃ አይኖርም የሚሉት ምሁሩ በምክክር ወቅት ሁሉም እኩል ኾኖ ነው የሚቀመጠው፣ ይሄን ሁሉም ማመን አለበት ነው ያሉት።
ለስኬታማ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከዝግጅት እስከ ፍፃሜ ድረስ ያለውን አካሄድ ማስተካከል፣ በእኩልነት ማሳተፍ ግድ እንደሚልም አንስተዋል። ሕዝብ ብሔራዊ ምክክር ኮሚሽኑን ስኬታማ እንዲኾን በማድረግ አሁን ካለበት ችግር እፎይ ማለት ይገባል ነው ያሉት። ኮሚሽኑ ከተጽዕኖ ነፃ ከኾነ 50 በመቶ ሥራው እንደሚቀጥልም ተናግረዋል። ተቋሙ ገለልተኛ ኾኖ ከሠራ የኢትዮጵያን ችግሮች እንደሚፈቱም ገልጸዋል። ለገለልተኝነት ትኩረት መስጠት እና ያልተቋረጠ ድጋፍ ማድረግ ለስኬታማነቱ ታላቅ አስተዋጽኦ አለው።
እርስዎስ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑን ደግፈው እና ሂደቱን አሳምረው የኢትዮጵያን ችግር በመፍታት አስተዋጽኦ ያደርጉ ይኾን? በእርስዎ መልካም አስተዋጽኦ መልካም ውጤት ይገኛልና።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!