
ሰቆጣ: የካቲት 21/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ከመቸውም ጊዜ በላይ የክልሉን ብሎም የኢትዮጵያን ሰላም በዘላቂነት ለማስጠበቅ መዘጋጀታቸውን በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር የተመደቡ የቀድሞ የልዩ ኃይል አባላት ገለጹ።
ረዳት ሳጅን ሙሐባው አባተ የተሰጠው ሥልጠና የነበረውን የተዛባ አመለካከት ቀይሮታል ብሏል። ከሥልጠና እስከተመደቡበት ቦታ ድረስ ሕዝቡ በፍጹም ክብር እንደተቀበላቸውም ነው ያስረዳው፡፡ ሰላም ወዳዱን የአማራ ሕዝብ ለማገልገልም መዘጋጀቱንም ገልጿል።
ኮንስታብል ሚሚ እያያው ሥልጠናው ልዩነቶችን በጋራ መፍታት ባሕል እንዲኾን እና የሀገሪቱን ታሪክ ለማወቅ እንዳስቻላት ተናግራለች። ችግሮችን በኃይል ለመፍታት የሚሠሩ ቡድኖች ወደ ተሐድሶ ሥልጠና ገብተው በድጋሜ ሀገራቸውን ለመካስ የተሰጣቸውን እድል እንዲጠቀሙ ኮንስታብል ሚሚ አሳባለች።
ምክትል ኢንስፔክተር መብራቱ አቤ ኢትዮጵያን ከገባችበት የሰላም እጦት ለማውጣት እንደሚሠሩ ገልጸዋል። የዋግ ኽምራ ማኅበረሰብ ላደረገላቸው አቀባበልም አመሥግነዋል።
የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ሰላም እና ጸጥታ መምሪያ ኀላፊ ሀምሳ አለቃ አዘዘው አዳነ የጸጥታ አካላቱ በዋግ ኽምራ መመደባቸው ያለውን አንጻራዊ ሰላም የበለጠ ያጠነክረዋል ብሏል። ሰላም ወዳዱ የዋግ ሕዝብ በፍቅር እንደተቀበላቸው በቀጣይም ከጸጥታ አካላቱ ጎን እንዲቆም አሳስበዋል።
የቀድሞው የልዩ ኀይል አባላት ሰቆጣ ከተማ ሲገቡ የብሔረሰቡ ከፍተኛ የሥራ አመራሮች እና የሰቆጣ ከተማ ነዋሪዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ አቀባበል አድርገውላቸዋል።
ዘጋቢ፡- ደጀን ታምሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!