የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ እና ለማቋቋም እየሠራ እንደሚገኝ የሰላም ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

44

አዲስ አበባ: የካቲት 21/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የፌዴራል መንግሥት ከክልሎች ጋር በመተባበር ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለው የሚገኙ ዜጎችን በአጠረ ጊዜ ወደ ቀያቸው ለመመለስ እና ለማቋቋም እየሠራ እንደሚገኝ የሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዱአለም ገልጸዋል። ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከክልሎች ጋር በመተባበር የሀገር ውስጥ ተፈናቃይ ዜጎችን ወደ ቀድሞ ቀያቸው ለመመለስ እና በዘላቂነት ለማቋቋም ያለመ የውይይት መድረክ አካሂዷል።

በመድረኩ መልእክት ያስተላለፉት የሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዱዓለም በተለያዩ ግጭቶች ምክንያት ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለው በብዙ ችግሮች ውስጥ እያለፉ የሚገኙ ዜጎችን ወደ ቀያቸው መልሶ በዘላቂነት የማቋቋም ሥራ የመንግሥት ትልቅ የትኩረት አቅጣጫ መኾኑን ተናግረዋል።

ሚኒስትሩ እስካሁን ባለው ሂደት ዜጎችን ወደ ቀያቸው የመመለስ ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝ ገልጸው ውጤት የታየባቸው ክልሎችም እንዳሉ አንስተዋል። የፌዴራል መንግሥት ከክልሎች ጋር በመተባበር ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለው የሚገኙ ዜጎችን በአጠረ ጊዜ ወደ ቀያቸው ለመመለስ እና ለማቋቋም እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በመድረኩ ላይ ”የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀድሞ ቀያቸው የመመለስ እና በዘላቂነት የማቋቋም እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት በሰላም ሚኒስቴር የግጭት አሥተዳደር መሪ ሥራ አስፈጻሚ ይርጋለም መንግሥቱ ቀርቧል፡፡

በሌላ በኩል የኦሮሚያ እና የአማራ ተፈናቃዮች ሪፖርትን በተመለከተ ከሁለቱ ክልሎች በመጡ ተወካዮች ቀርቧል።በውይይቱ የተገኙ ተሳታፊዎች ተፈናቃይ ዜጎችን ወደ ቀያቸው ከመመለስ አንፃር እያጋጠሙ ያሉ የአመለካከት፣ የፀጥታ እና የበጀት ችግሮች በስፋት ማንሳታቸውን ከሰላም ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን አገልግሎቱን ቀልጣፋ ለማድረግ ከተቋማት ጋር በጋራ ለመሥራት የትብብር ስምምነት ተፈራረመ።
Next articleየክልሉን ሰላም በዘላቂነት ለማስጠበቅ መዘጋጀታቸውን የቀድሞ ልዩ ኃይል አባላት ገለጹ።