
አዲስ አበባ: የካቲት 21/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን የካፒታል ገበያ መሠረተ ልማቶችን ለማጠናከር፣ ግልጽነትን ለማጎልበት እንዲሁም የቴክኖሎጂ አቅምን ለማዳበር የሚረዱ ሁለት ስምምነቶችን ተፈራርሟል።
የመጀመሪያው ስምምነት የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ተአማኒነት ግብረ ኃይል የትብብር እና ቅንጅት የመግባቢያ ስምምነት በፍትሕ ሚኒስቴር ፣ በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ፣ በኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ፣ በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን እንዲሁም በፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት መካከል የተደረገ ነው።
የዚህ ስምምነት ዐቢይ ዓላማም የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያን ሕጋዊ እና ከወንጀል ድርጊቶች የጸዳ ለማድረግ በተቋማቱ መካከል ቋሚ እና ቀልጣፋ ቅንጅታዊ የአሠራር ሥርዓት ለመዘርጋት እንዲሁም ውጤታማ የሕግ ማስከበር ሥርዓት በመፍጠር የካፒታል ገበያውን ተአማኒነት ማረጋገጥ ነው ተብሏል።
ግብረ ኃይሉ ማጭበርበር ባለበት ሁኔታ እና በሕገ ወጥ የአክሲዮን አቅርቦት ላይ የተሰማሩ እና በርካታ ኢንቨስተሮች ያላግባብ ገንዘባቸውን እንዲያወጡ ምክንያት የኾኑ አክስዮን ሻጮችን በመለየት ለፍርድ የማቅረብ ኀላፊነት አለበት ተብሏል።
ሁለተኛው ስምምነት የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለሥልጣንን በቴክኖሎጂ ለመደገፍ የተደረገ የትብብር መግባቢያ ስምምነት ሲኾን ስምምነቱ በየኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ፣ በኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጄንሲ፣ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት እና በኢትዮጵያ ብሔራዊ መታወቂያ አገልግሎት መካከል የተደረገ ነው።
ከሳይበር ደኅንነት ጋር የተያያዙ የቴክኖሎጂ ድጋፎችን ያካተተው ይህ ስምምነት የባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱን የገበያ መቆጣጠር እና የኢንቨስተሮችን ደኅንነት የመጠበቅ አቅሙን ለማሳደግ ያለመ መኾኑን የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ብሩክ ታዬ (ዶ.ር) ተናግረዋል።
ስምምነት እና የተግባር ሂደቱም ቴክኖሎጂን በመጠቀም ሊከሰቱ የሚችሉ አደጋዎችን በንቃት ለመከታተል እና ለመቅረፍ እንዲሁም አጠቃላይ የቁጥጥር ማዕቀፉን ለማሳደግ ታላሚ ያደረገ ነው ተብሏል።
ዘጋቢ፡- እንዳልካቸው አባቡ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!