
ጎንደር: የካቲት 21/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የተገልጋዩችን እርካታ ለመጨመር እየሠራ መኾኑን የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ከተማ እና መሰረተ ልማት መምሪያ አስታውቋል።
በጎንደር ከተማ አሥተዳደር የከተማ እና መሰረተ ልማት መምሪያ በዘርፉ ያለውን የአገልግሎት አሰጣጥ ለማዘመን የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።
መምሪያው የአገልግሎት ፈላጊዎችን እርካታ ለመጨመር የአንድ ማዕከል የሥራ አሥኪያጅ ችሎት አቋቁሞ እየሠራ ይገኛል። ተቋሙ የሥራ አሥኪያጆች የችሎት የማስጀመሪያ መርሐ ግብሩንም በዛሬው ዕለት አካሂዶል። ችሎቱ ከተገልጋዮች የሚነሱ አቤቱታዎች በአዳራሽ በጋራ ተቀብሎ በጋራ መፍትሔ የሚሰጥበት መንገድ ነው።
ችሎቱ ከባለ ጉዳዮች የሚነሱ ጥያቄዎችን ፊት ለፊት በሚመለከታቸው የተቋሙ ሥራ አስኪያጆች ምላሽ የሚሰጥበት ሂደት ነው። የአንድ ማዕከል የችሎት አገልግሎቱ በአንድ ሳምንት ሁለት ቀን ተግባራዊ ይደረጋልም ተብሏል።
በመርሐ ግብሩ የተገኙ አስተያየት ሰጭ ተገልጋዮች እንዳስታወቁት ከአሁን በፊት የከተማ አሥተዳደሩ ከተማ እና መሰረተ ልማት መምሪያ አገልግሎት አሰጣጡ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮች ሰፊ እንደነበሩ አንስተዋል።
በአዲስ ተግባራዊ የሚደረገው ችሎቱ በተገልጋዮች ዘንድ ሲነሱ የነበሩ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ለመፍታት የጎላ ሚና እንደሚጫወት እና የደንበኞችን እርካታ ለመጨመር የሚያስችል መኾኑንም ተናግረዋል።
ተቋሙ ከተገልጋዮች የሚመጡ አቤቱታዎችን በጥሞና አድምጦ የሚመለካታቸው ሥራ አስኪያጆች በአንድ ማዕከል ተገኝተው እልባት የሚሰጡበት ሂደት መኾኑን ተናግረዋል፡፡
ዘርፈ ብዙ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል መኾኑንም የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ከተማ እና መሰረተ ልማት መምሪያ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አንዱዓለም ሙሉ በመርሐ ግብሩ ተናግረዋል።
ችሎቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል እና የተገልጋዮችን እርካታ እንዲጨምርም ቀጣይነት ያለው ክትትል እና ድጋፍ እንደሚደረግም አቶ አንዱዓለም አስታውቀዋል።
ዘጋቢ:- ምስጋነው ከፍ ያለው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!