
አዲስ አበባ፡ የካቲት 21/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ባለሃብቶች በክልሉ ያለው የኢንቨስትመንት ፖሊሲ አሳሪ እና አጓጊ ባለመኾኑ በርካታ ኢንቨስተሮች ክልሉን በሚፈለገው ልክ እንዳያለሙ እንቅፋት መኾኑን አንስተዋል።
የፖሊሲ ማሻሻያዎችን በማድረግ ሳቢ የልማት ሥነ ምህዳርን የክልሉ አመራር መፍጠር እንዳለበት ያነሱት ባለሃብቶቹ የመሰረተ ልማት ችግሮች እንዲቀረፉላቸውም ጠይቀዋል።
የክልሉ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በሰጡት ምላሽ የክልሉን ሕዝብ ጥያቄ ለመመለስ በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል። በክልሉ ያሉ ግጭቶችን ለመፍታት አሁንም የሰላም ንግግሮችን ለማድረግ የክልሉ መንግሥት ቁርጠኛ መኾኑን ተናግረዋል።
የክልሉ መንግሥት የፀጥታ ችግር ከማጋጠሙ ቀደም ብሎ ጀምሮ በውይይት ግጭቱን ለማስቀረት ጥረቶች ሲያደርግ እነደነበር ገልጸዋል፡፡ ርእሰ መሥተዳድሩ ለሰላም መቼም እንደማይረፍድ በመረዳት እና የሚከፈለውን መስዋዕትነት ለማስቀረት ከፌደራል መንግሥቱ ጋር እየተሠራ ነው ብለዋል። ለክልሉ ልማት ትልቅ ተግዳሮት እየፈጠረ የሚገኘውን የሰላም እጦት እልባት ለመሥጠት እንደሚሠራ ገልጸዋል። ባለሃብቶች የክልሉን ልማት እንዲያፋጥኑም አደራ ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ቤተልሄም ሰሎሞን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!