ለአህጉራዊ ምጣኔ ሃብት መሳለጥ እና ለነፃ ንግድ ቀጣና ከፍተኛ ፋይዳ አለው የተባለለት የኢ-ኮሜርስ ማዕከል ወደ አገልግሎት መግባቱ ተገለጸ፡፡

32

አዲስ አበባ: የካቲት 21/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የካርጎ አገልግሎቱን ለማሳለጥ በቦሌ ዓለም ዓቀፍ አየር ማረፊያ በ50 ሚሊዮን ዶላር ያስገነባውን የኢ-ኮሜርስ ማዕከል አስመርቋል። በመረሐ -ግብሩ ላይ የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜ (ዶ.ር)፣ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ.ር)፣ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ሰመሪታ ሰዋሰው፣ የአየር መንገዱ የቦርድ አባላት፣ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች፣ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ እንዲሁም የካርጎ ተጠቃሚ ዓለም አቀፍ አስመጪ እና ላኪዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው አየር መንገዱ በዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነቱን ለማስቀጠል ዘመናዊ አሠራሮችን መተግበሩን ቀጥሏል ብለዋል።
በዓለም ላይ የዲጂታል ግብይት እያደገ በመምጣቱ የመደበኛው ካርጎ አገልግሎት እየቀነሰ በአንጻሩ የኢ-ኮሜርስ የካርጎ አገልግሎት እየሰፋ መምጣቱን ጠቅሰው ለዚህም አየር መንገዱ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ መኾኑን ጠቅሰዋል።

ለዚህም የካርጎ አገልግሎቱን ለማሳለጥ በቦሌ ዓለም ዓቀፍ አየር ማረፊያ በ50 ሚሊዮን ዶላር በ15 ሺህ ስኩዌር ሜትር ላይ ሦስተኛውን እና ለኢ-ኮሜርስ የሚውል ዘመናዊ የካርጎ ማዕከል ማስገንባቱን ገልጸዋል።

በኤሌክትሮኒክስ ግብይት ሥርዓት የሚገዙ እቃዎችን ወደ ተለያዩ የዓለም ሀገራት በአዲስ አበባ በኩል ለማጓጓዝና የገበያ ትስስሩን ይበልጥ ለማጠናከር እንደሚያስችልም ጠቅሰዋል።
የካርጎ ማዕከሉ የተለመደ አገልግሎት የሚሰጥ ብቻ ሳይኾን ዓለም እየሄደበት ያለውን አዲስ የገበያ ስልት ለማሳለጥ ቁልፍ ሚና ያለው መኾኑንም ዋና ሥራ አስፈፃሚው ገልጸዋል።
የተገነባው የኢ-ኮሜርስ ማዕከል ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይኾን ለአህጉራዊ ምጣኔ ሃብት መሳለጥ እና ለነፃ ንግድ ቀጣና ከፍተኛ ፋይዳ ያለው መኾኑንም አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአጠቃላይ ገቢው ከ30 እስከ 35 በመቶ የሚሠበሥበው ከካርጎ አገልግሎት መኾኑን ገልጸው የዘርፉን አቅም ይበልጥ ለማጎልበት እየተሠራ ነው ብለዋል።
በዚህም የአየር መንገዱ የጭነት አገልግሎት ከዓመት ዓመት እያደገ መምጣቱን ነው የገለጹት።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባለፈው በጀት ዓመት ካስገነባው አጠቃላይ 6 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር ገቢ 2 ቢሊዮን ዶላር የሚኾነው በካርጎና ሎጂስቲክ አገልግሎት ያስገባው ነው።
በቅርቡም የ2023 ምርጥ የካርጎ እና ሎጅስቲክስ ኦፕሬተር እንዲሁም የአፍሪካ ምርጡ የካርጎ ኦፕሬተር በሚል አየር መንገዱ በሁለት ዘርፎች ለአምስተኛ ጊዜ መሸለሙ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው የኢ-ኮሜርስ ማዕከል ግንባታው በአጭር ጊዜ ተጠናቅቆ ወደ ሥራ እንደሚገባ በቅርቡ ለኢዜአ መግለጻቸው ይታወሳል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየሴቶች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ ታቅዶ መሠራት እንዳለበት የአማራ ክልል ምክር ቤት የሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።
Next articleየሰሜን ሸዋ ዞን መንገድ መምሪያ የ2016 በጀት ዓመት የ3 ድልድዮችን ግንባታ ሊያስጀምር ነው።