
ባሕር ዳር: የካቲት 21/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ሠራተኞች እና የምክር ቤቱ የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎች ዓለም አቀፉን የሴቶች ቀን (ማርች8) በተለያዩ ኹነቶች አክብረዋል።
በበዓሉ የተሳተፉት የአማራ ክልል ምክር ቤት የሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እመቤት ከበደ የቀኑ መከበር በሁለንተናዊ ዘርፍ የሴቶችን ተሳትፎ ለማረጋገጥ በየደረጃው ያለችውን ሴት እያሰብን እንድንሠራ ያስችለናል ብለዋል።
“ቀኑን ስናከብር የሴቶች የትምህርት ተሳትፎ እና የምጣኔ ሃብት ተጠቃሚነት እንዲጨምር፣ የሥራ ዕድል እንዲፈጠርላቸው እና የቁጠባ ባሕላቸው እንዲጎለብት በየደረጃው ያለ አመራር አስቦ እንዲሠራ እንደሚያስችል” ነው የቋሚ ኮሚቴዋ ሰብሳቢ የገለጹት።
መሬታቸውን የሚነጠቁ፣ ጾታዊ ጥቃት የሚደርስባቸውን እና ለሌሎች ችግሮች ተጋላጭ የኾኑትን ሴቶች በሚቻለው ሁሉ በማገዝ መብታቸውን ማክበር እና ተጠቃሚነታቸውን ማሳደግ እንደሚገባም ጠቅሰዋል። ይህ ኀላፊነትም ለአንድ አካል ብቻ የሚተው ሳይኾን የሁሉንም ዜጋ ተሳትፎ እና ርብርብ እንደሚፈልግ ጠቁመዋል።
ዘንድሮ በክልላችን የተፈጠረው ውስጣዊ ችግር እንዲፈታ ሴቶች መቻቻልን፣ መወያየትን እና መፍትሔን ማሰብ ይጠበቅብናል ያሉት ወይዘሮ እመቤት በውይይት እንጂ በኃይል የሚፈታ ችግር ስለሌለ በውይይት በማመን ለሰላም መሥራትም እንደሚጠበቅ አሳስበዋል።
በበዓሉ የኤች አይ ቪ/ ኤድስ ሥርጭት፣ ጉዳት እንዲኹም መከላከል ላይ የመወያያ ሃሳብ ቀርቧል። በሽታው የተሰጠው ትኩረት እየቀነሰ በመኾኑ ሥርጭቱ እየጨመረ መኾኑ፣ በዚህም ሴቶች እና ሕጻናት የበለጠ ተጋላጭ መኾናቸው ተነስቷል። ጤና ቢሮ፣ አጋር አካላት እና ምክር ቤቱ ተደጋግፈው ለችግሩ መቀነስ መሥራት እንደሚገባቸውም ተመላክቷል።
ዘጋቢ:- ዋሴ ባየ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!