
አዲስ አበባ: የካቲት 21/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ እና ኬንያ በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ሰላምና ደህንነትን ማረጋገጥ እና የኢኮኖሚ ትብብርን ማጠናከር በሚችሉበት ሁኔታ ላይ መምከራቸውን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ.ር) ገልጸዋል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የኬንያ ጉብኝትን አስመልክቶ ሚኒስትሩ በሰጡት ማብራሪያ “ኢትዮጵያና ኬንያ ረጅም ጊዜ የቆየ የትብብር፣ የአጋርነት እናየወንድማማችነት ኅብረት አላቸው” ብለዋል፡፡
ቀደምት መሪዎች በሠሩት ሥራ በሀገራቱ መካከል ግጭቶች እንደሌሉ በመግለጽ፤ የሁለቱ ሀገራት መሪዎች በሁለትዮሽ ትብብር ላይ ሰፊ ውይይት ማካሄዳቸውን አስታውሰዋል፡፡
በውይይታቸው በተለይም ቀደም ሲል በአዲስ አበባ የኢትዮ-ኬንያ የሚኒስትሮች ጥምር ምክር ቤት በደረሰው ስምምነት መሰረት ሀገራቱ ሰባት ስምምነቶችን እንደተፈራረሙ አንስተዋል፡፡
ስምምነቱ በማኅበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊ እና በደህንነት ጉዳዮች ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ ጠቅሰዋል። ቀደም ባሉት ጊዜያትም የተፈረሙ ስምምነቶች የሚጠናከሩበት እና የሚሰፉበት ጉዳይ ላይ እንደመከሩ ገልጸዋል፡፡
ሀገራቱ በምሥራቅ አፍሪካ የሚገኙ በመሆናቸው ከተለዋዋጩ እና ከአዳጊው የዓለም ሁኔታ ጋር በሚያድግ መልኩ የሁለቱ ሀገራት የደህንነት ሁኔታ መጠናከር በሚችልበት ላይም መምከራቸውን ጠቁመዋል፡፡
በተለይም በቀጣናው እንደስጋት የሚታየው አልሸባብ በሁለቱም ሀገሮች ላይ ጥቃት የሚፈጽም በመሆኑ ይሄንን በጋራ በሚመክቱበት እንዲሁም ሰላምና ደህንነትን ማረጋገጥ በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ተወያይተዋል ነው ያሉት፡፡
በተጨማሪም የኢኮኖሚ ትብብር ግንኙነቱ የሚጠበቀውን ያህል አለመሆኑን አንስተው በዘርፉ ላይ ያለው ግንኙነት በሚጠናከርበት ሁኔታ ላይ ምክክር ተደርጓል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለኬንያ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ ኬንያም ከኢትዮጵያ ገዝታ ለመጠቀም ከስምምነት ላይ ተደርሶ የኤሌክትሪክ ማሰራጫ መስመሮችም ተዘርግተዋል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ የወደብ አማራጮቿን እያሰፋች ነው ያሉት ሚኒስትሩ “የሁለቱ ሀገራት መሪዎች በመንገድ አቅርቦት እንዲሁም በዲጂታል ኢኮኖሚና ደህንነት ላይ በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን ውይይት አካሂደዋል” ብለዋል፡፡
ድህነትን ለማስወገድ የሀገራቱን የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ማጠናከር፣ የአቅም ግንባታ ሥራዎችን ማጎልበት እንዲሁም የጥናትና ምርምር ሥራዎችን በጋራ ለመሥራት የሚያስችል ውይይት መካሄዱንም ተናግረዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!