የዓድዋ ድል መታሰቢያ በዓል በሰላም እንዲከበር አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ማድረጉን የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል አስታወቀ ።

46

አዲስ አበባ: የካቲት 21/2016 ዓ.ም (አሚኮ) 128ኛው የዓድዋ ድል መታሠቢያ በዓልን ለማክበር የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ፍፁም ሠላማዊ እንዲሆኑ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት አጠናቆ ወደ ስራ መግባቱን የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ሃይል አስታውቋል። በዓሉ ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲከበር ለማስቻል በወጣው የማስፈጸሚያ እቅድ ላይ በአዲስ አበባ ፖሊስ ሰላም አዳራሽ ላይ ውይይት ተደርጓል።

የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት የልዩ ዘመቻ ኀላፊ ጄኔራል ተስፋዬ አያሌው በውይይቱ ወቅት እንደገለጹት የመላው ኢትዮጵያውያን በዓል የሆነው የዓድዋ ድል በዓል ሲከበር ምንም አይነት ስጋት እንዳያጋጥም የፀጥታ ኃይሉ ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል። የበዓሉ ተሳታፊዎች ጸብን ከሚያነሳሱ እና በዓሉን የማይገልፁ ልዩ ልዩ እንቅስቃሴዎችን ከመፈጸም ሊታቀቡ ይገባል ብለዋል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው በበኩላቸው የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም ታሪኩን በሚመጥን መልኩ ተገንብቶ በተጠናቀቀበት ወቅት መከበሩ የዘንድሮውን የዓድዋ ድል በዓልን ልዩ እንደሚያደርገው አስታውሰው በዓሉ ፍፁም ሰላማዊ በሆነ መንገድ ተከብሮ እንዲውል አስፈላጊው ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አሥተዳደር ቢሮ ኀላፊ ሊዲያ ግርማ እንደተናገሩት ለ128ኛ ጊዜ የሚከበረውን የዓድዋ ድል መታሰቢያ በዓልኔ የሚያውኩ ሁኔታዎች እንዳያጋጥሙ በመዲናችን ስጋት ሊሆኑ የሚችሉ ነገሮችን በማጥናትና በመለየት ችግሩን ለማስወገድና ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል ዝግጅት ተደርጓል ።

በፌዴራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ የኦፕሬሽን ዋና መምሪያ ኀላፊ ምክትል ኮሚሽነር አበራ ሁንዴ በበኩላቸው የዓድዋ ድል በዓል መከበርን እንደ ጥሩ አጋጣሚ በመጠቀም ሁከት ለመፍጠርና የግል ፍላጎታቸውን ለማንፀባረቅ የሚሞክሩ አካላት በሚያጋጥሙበት ወቅት ለፀጥታ ኃይሉ በመጠቆም ኅብረተሰቡ እና የበዓሉ ተሳታፊዎች የተለመደ ትብብራቸውን ማድረግ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል ።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከፖላንድ የመጡ የሕክምና ባለሙያዎች በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ነጻ የሕክምና አገልግሎት እየሰጡ ነው።
Next articleኢትዮጵያን በውኃ ሀብቶቿ ተጠቃሚ ማድረግ የሁሉም ኀላፊነት መኾኑን የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ጅፋር በድሩ ገለጹ፡፡