“በሀገራችን ሰላም እና ልማት እንዲፋጠን ሴቶች አስተዋጽኦ እናበርክት” አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ

51

ባሕር ዳር፡ የካቲት 21/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ማርች 8 ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን በውይይት እያከበረ ነው።

በውይይቱ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የአማራ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፋንቱ ተስፋዬ የሴቶች ቀን በየዓመቱ መከበሩ ሴቶች እየተመካከርን እና እየተራረምን ችግሮቻችንን እንድንቀርፍ ያግዘናል ብለዋል። ከግማሽ በላይ የኾኑ ሴቶችን ተሳትፎ በማሳደግ ማኅበራዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊ እና ፖለቲካዊ ተጠቃሚም እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ለ46ኛ፣ በአማራ ክልል ለ29ኛ ጊዜ የምናከብረው በዓል “ሴቶችን እናብቃ ልማት እና ሰላምን እናፋጥን” በሚል መሪ መልዕክት ይከበራል፡፡ ልጅ ማሳደግ እና ቤተሰብን መምራት የጋራ ቢኾንም ሴቶች ከሰላም ጋር ያለንን ቅርበት በመጠቀም ለሰላም መሥራት ይጠበቅብናል ብለዋል።

“በሀገራችን ሰላም እና ልማት እንዲፋጠን ሴቶች አስተዋጽኦ እናበርክት” ብለዋል አፈጉባኤዋ። በዓሉን በዓመት አንድ ቀን በማክበር ብቻ ሳይኾን ዓመቱን በሙሉ የሴቶችን ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት አልሞ መሥራት እንደሚጠበቅም ገልጸዋል።

ሴቶች በሰላምም በልማትም ተሳትፏቸውን ለማዳበር የአመለካከት ችግራቸውን ማስወገድ ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡ አፈ ጉባኤ ፋንቱ በተሰማሩበት የሥራ መስክ ብቁ እና ተወዳዳሪ ኾነው በራስ መተማመንን መፍጠር እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል።

እርስ በእርስ የመረዳዳት እና የማጠናከርን አሠራር በማበጀት አቅምን መገንባት ያስፈልጋል። ተሳትፎ እና እኩል ተጠቃሚነት በችሮታ የምናገኘው ሳይኾን በብቃት እና በአበርክቶ መኾን ይገባዋል ብለዋል። በዓሉን ስናከብር ከኔ ምን ይጠበቃል የሚለውን ማሰብ አለብን ብለዋል አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ።

ዘጋቢ፡- ዋሴ ባየ

Previous articleከዓድዋ ድል ተምረን ችግሮቻችንን መፍታት የዛሬው ትውልድ የቤት ሥራ መሆን እንዳለበት ተገለጸ።
Next articleከፖላንድ የመጡ የሕክምና ባለሙያዎች በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ነጻ የሕክምና አገልግሎት እየሰጡ ነው።