
ባሕር ዳር: የካቲት 21/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ለፓን-አፍሪካዊነት ማበብ ትልቅ አበርክቶ የነበረው የኢትዮ-ጋና ግንኙነት ከፖለቲካ ባሻገር በኢኮኖሚ እና ማኅበራዊ መስኮችም ሊጠናከር እንደሚገባው በአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ከፍተኛ የሕግ አማካሪው አሕመድ ቡግሪ (ዶ.ር) ገልጸዋል። ዶክተር አሕመድ ኢትዮጵያ የጥቁሮች ብቻ ሳትኾን የሰው ዘር መገኛ እና የነጻነት ምልክት ናት ብለዋል።
ጋና ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ ከባርነት ቀንበር የተላቀቀች የጥቁሮች አብሪ ኮከብ መኾኗን ገልጸዋል፡፡ በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ጋናን ጨምሮ ለአፍሪካ ሀገራት ነጻነት ንቅናቄ ሁነኛ ምልክት በመኾን ማገልገሏን ተናግረዋል።
ሁለቱ ለፓን አፍሪካዊነት ማበብ ትልቅ አበርክቶ የነበራቸው ሀገራት መኾናቸውንም ጠቁመዋል፡፡ ኢትዮጵያ ይህን ዕድል ለትውልድ ግንባታ መጠቀም እና የአፍሪካውያን ማዕከልነቷን ማጽናት አለባት ብለዋል።
ሁለቱ ሀገራት ጠንካራ ፖለቲካዊ ትስስር እና የሁለቱ ሀገራት ሕዝቦችም የሚያመሳስላቸው ታሪክ እና ሥነ-ልቦና ያላቸው መኾናቸውን አንስተዋል።
በመኾኑም የአፍሪካ ነጻ ንግድ ቀጣናን እና ሚሊዮኖችን ባስተሳሰረው የኢትዮጵያ አየር መንገድን እንደ ዕድል በመጠቀም የሁለትዮሽ እና የሕዝብ ለሕዝብ ትስስራቸውን ማጎልበት እንደሚገባቸው ገልጸዋል።
የፓን አፍሪካዊነት ፅንሰ ሃሳብ አፍሪካ በአፍሪካውያን የተገነባች ትኾን ዘንድ በቀደሙት አባቶች የተጀመረው እና የዛሬው ትውልድም ሊመራበት የሚገባው እሳቤ እንደኾነ ዶክተር አሕመድ ተናግረዋል።
የጋና ነጻነት መሪ እና የነጻይቱ ሀገር መሪ ፕሬዚዳንት ክዋሚ ንኩርማ፣ ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴና ሌሎች ቀደምት መሪዎች አንድ የተባበረች አፍሪካን የመገንባት ህልም ነበራቸው ይላሉ።
ይህን የፓን አፍሪካዊነት እሳቤ ቀጣዩ ትውልድ በቅኝ ግዛት ልቦና ውቅር ተጽዕኖ በመውደቁ ለመከፋፈልና ለተናጠላዊ ሉዓላዊነት ትኩረት እንዳደረገው አስረድተዋል።
አፍሪካውያን የተሟላ ሉዓላዊነት የሚኖራቸው በተሳሰረች እና አንድነቷ በተጠበቀ አፍሪካ ጥላ ሥር እንጂ በተናጠል አካሄድ ባለመኾኑ ከ60 ዓመታት በኋላም ወጣቱ ትውልድ ሊያቀነቅነው እንደሚገባ አንስተዋል።
የአፍሪካውያን ትምህርት ከቅኝ ግዛት እና ባርነት ትርክት ባሻገር ከአውሮፓውያን ሥርዓተ ትምህርት የተፋታ የራሷ ባሕል፣ ታሪክ እና ፓን አፍሪካዊነት መልክ ባለው ትምህርት ትውልድን መቅረጽ እንደሚገባ ተናግረዋል።
የአፍሪካ ኅብረት የቀድሞ መሪዎችን ሐውልት ማቆሙ ፓን አፍሪካዊነትን ለዚህ ትውልድ ለማስተማር እና ህልማቸውን ለማጋባት ትልቅ ሚና እንደሚኖረውም ገልጸዋል።
ከዶክተር ክዋሚ ንኩርማ ጀምሮ ለቀዳማዊ አጼ ኅይለሥለሴ እና ዘንድሮ ደግሞ ለጁሊዬስ ኔሬሬ በተለያዩ አቅጣጫዎች መታሰቢያ ሐውልት መቆሙ አንዱ ትውልድን በፓን አፍሪካኒዝም መንፈስ ለማነጽ አጋዥ መሣሪያ ነው ሲል ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!