
ባሕር ዳር: የካቲት 21/2016 ዓ.ም (አሚኮ) መደበኛ ያልኾነ ፍልሰትን ከምንጩ ለማስቆም በጥምረት እየተሠራ መኾኑን የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጿል። የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት(IOM) ሪጅናል ዳይሬክተር ራና ጃበር እና በኢትዩጵያ ቺፍ ኦፍ ሚሽን ከኾኑት አቢባቱ ዋኔ ጋር ተወያይቷል።
በውይይቱ በሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚንስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ.ር) መደበኛ ያልኾነ ፍልሰትን በመከላከል፣ የተመላሽ ዜጎችን ጥበቃ እና መልሶ ማቋቋም ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ጥረት እያደረገች መኾኑን ተናግረዋል።
ከነዚህም ተግባራት መካከል መደበኛ ባልኾነ መልኩ ለስደት የተጋለጡ ዜጎችን ወደ ሀገራቸው ከመጡ በኋላ ወደ መጡበት አካባቢ የመመለስ ሥራ በስፋት እየተሠራ መኾኑን ጠቅሰዋል።
ፍልሰትን መካላከል ላይ ያተኮሩ ሥራዎች እና ኢትዮጵያ ለዜጎቿ ምቹ ሀገር እንድትኾን መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንደኾነም ተናግረዋል።
ተመላሽ ዜጎች በተለይም ወላጆቻቸውን በስደት ላጡ ሕጻናት፣ ሴቶች ተገቢውን ድጋፍ አግኝተው መልሰው ስለሚቋቋሙበት ሁኔታ እና ዘላቂ የሆኑ የመጠለያ አገልግሎት የሚሰጡ ማዕከላትን ማስፋፋት ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ.ር) አሳስበዋል።
ሚኒስትሯ መደበኛ ያልኾነ ፍልሰት በኢትዮጵያ እና በዜጎቿ ላይ እያስከተለ ያለውን የሰብዓዊ ቀውስ ለመቀነስ በሚያስችሉ ሁኔታዎች ላይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ እንደ ዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት( IOM) ካሉ ተቋማት ጋርም በትብብር እና በቅንጅት መሥራቱን እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።
የዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት( IOM)ሪጅናል ዳይሬክተር ራና ጃበር በበኩላቸው ኢትዮጵያ መደበኛ ያልኾነ ፍልሰትን በመከላከል፣ የፍልሰት ተጎጂዎችን በመደገፍ እና መልሶ በማቋቋም እያደረገች ያለችውን ጥረት አድንቀዋል።
ድርጅቱ ኢትዮጵያ የተመላሽ ዜጎችን ጥበቃ እና መልሶ ማቋቋም ጋር በተያያዘ ለምትሠራው ሥራ እገዛ እንደሚያደርግም መግለጻቸውን ከሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ዋቢ አድርጎ ኢቢሲ ዘግቧል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!