“ከአራት ሚሊዮን ኩንታል በላይ የሩዝ ምርት ተሠብሥቧል” የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ

43

ባሕር ዳር፡ የካቲት 21/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በ2015/16 ዓ.ም በጀት ዓመት 4 ሚሊዮን 188 ሺህ ኩንታል የሩዝ ሰብል መሠብሠቡን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አስታውቋል፡፡

በአማራ ክልል በዚህ ዓመት 101 ሺህ 883 ሄክታር መሬት በሩዝ ሰብል በመሸፈን ከ5 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሠብሠብ ታቅዶ እንደነበር የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ሰብል ልማት እና ጥበቃ ዳይሬክተር ማንደፍሮ አስላከ (ዶ.ር) ተናግረዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ 82 ሺህ 279 ሄክታር መሬት በዘር በመሸፈን 4 ሚሊዮን 188 ሺህ ኩንታል የሩዝ ምርት መሠብሠቡን ተናግረዋል፡፡ ምርታማነቱም በሄክታር 50 ኩንታል እንደነበረ ገልጸዋል፡፡ ክልሉ ካሁን በፊት በሩዝ ምርት የማይታወቁ አካባቢዎችን እና ወረዳዎችን በማካተት መሥራቱንም ተናግረዋል፡፡

ካሁን በፊት ሩዝ ይመረትባቸው ከነበሩ የደቡብ ጎንደር ዞን ባለፈ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን እና በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር በማለማመድ ሥራ መሠራቱንም ጠቁመዋል፡፡

ሩዝ ሁለት ዓይነት ነው ያሉት ዳይሬክተሩ ውኃ በሚተኛበት ቦታ የሚመረት እና እንደማንኛውም ሰብል ውኃ በማይተኛበት ቦታ የሚመረት ተብሎ እንደሚከፈል ተናግረዋል፡፡

ዶክተር ማንደፍሮ አሁን ላይ እንደማንኛውም ሰብል የሚበቅለውን ሩዝ ለማስተዋወቅ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡ በተለይ የአፈር ዓይነታቸው እና ሥነ ምህዳራቸው ተስማሚ የኾኑ አካባቢዎችን የመለየት ሥራ እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡

“አሁን በስፋት የምናስተዋውቀው ውኃ በማይተኛበት አካባቢ የሚበቅለውን የሩዝ ዓይነት ነው” ብለዋል ዶክተር ማንደፍሮ፡፡ ሥራውን ከፎገራ ባልተናነሰ በሥፋት ለማምረትም ጥረት ይደረጋል ብለዋል፡፡

በዚህም በ2015/16 ዓ.ም ከተመረተው 83 ሺህ 279 ሄክታር መሬት ላይ 1 ነጥብ 2 በመቶ ጭማሪ የታቀደ ሲኾን ከምርት አንጻርም 16 ነጥብ 4 በመቶ ጭማሪ ለማምረት መታቀዱን ተናግረዋል፡፡

ሩዝ ከሌሎች ገበያ መር ምርቶች እንደ ስንዴ፣ ጤፍ እና በቆሎ ከመሳሰሉ ሰብሎች እንደሚወዳደርም ተናግረዋል፡፡ ሩዝ የክልሉ ትኩረት ኾኗል ያሉት ዶክተር ማንደፍሮ ፤ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ሩዝን በክላስተር ለማምረት ጥረት እያደረገ መኾኑንም ጠቁመዋል፡፡

የግብዓት አቅርቦቱ ለምርት ጭማሪው አስፈላጊ በመኾኑ አርሶ አደሮቹ ሁሉንም ፓኬጆች ተግባራዊ በማድረግ ምርታማነትን እንዲያሳድጉም አሳስበዋል፡፡ “አትላንራይስ” የተባለው የሩዝ ዝርያ ለአርሶ አደሮች እየተዋወቀ እና ግንዛቤ እየፈጠረ መኾኑንም ጠቁመዋል፡፡ የሩዝ ምርት ከዓመት ዓመት እየጨመረ ነው ያሉት ዶክተር ማንደፍሮ አርሶ አደሮችም ተጠቃሚነታቸው እያደገ መኾኑንም ጠቁመዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ኢትዮጵያን ከኬኒያ ያስተሳሰረውን የሱስዋ ኤሌክትሪክ ጣቢያ ጎበኙ።
Next articleመደበኛ ያልኾነ ፍልሰትን ከምንጩ ለማስቆም በጥምረት እየተሠራ መኾኑን የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።