በዋግ ኽምራ ያለውን የመንገድ ችግር ለመቅረፍ በትኩረት እየሠራ መኾኑን የብሔረሰብ አሥተዳደሩ መንገድ መምሪያ አስታወቀ።

20

ሰቆጣ፡ የካቲት 20/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ያለውን የመንገድ ችግር ለመፍታት በትኩረት እየሠራ መኾኑን የብሔረሰብ አሥተዳደሩ መንገድ መምሪያ አስታውቋል።

ከሰቆጣ – ጻግቭጂ ወረዳ የሚያገናኘው መንገድ በጦርነቱ ምክንያት ያጋጠመውን ችግር ተከትሎ የወረዳው ማኅበረሰብ ለከፍተኛ እንግልት ሲጋለጥ መቆየቱን ገልጸዋል። ወይዘሮ ዝይን ወልደሚካኤል የጻታ ከተማ ነዋሪ ሲኾኑ በመንገድ ችግር ምክንያት ሲሠሩት የነበረውን የንግድ እንቅስቃሴ እንዳቋረጡ ገልጸዋል።

ሥራቸውን እንዲቀጥሉም አሁን ላይ መንግሥት የጀመረው የመንገድ ጥገና በአፋጣኝ እንዲጠናቀቅ ጠይቀዋል። አቶ ቢምረው ረታ በወረዳው ባለው የመንገድ ችግር ምክንያት የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ስለማይገቡ በተገኙ ተሽከርካሪዎች ከፍተኛ ወጭ በማውጣት እና ከእቃ ላይ ተጭነው አገልግሎት እንደሚያገኙ ጠቁመዋል።

የጻግብጂ ወረዳ መንገድና ትራንስፖርት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሄኖክ ነይኑ ባለፉት ጊዜያት ባለው የመንገድ እና የጸጥታ ችግር ምክንያት ማኅበረሰቡ ለከፍተኛ እንግልት እና ወጭ ሲጋለጥ እንደነበር አስታውሰዋል።

በወረዳው 42 ኪሎ ሜትር መንገድ ተጠግኖ ለአገልግሎት ክፍት መኾኑን የገለጹት ኀላፊው ይህንን ተከትሎ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶብስ በየቀኑ መመደብ መጀመሩን ነው የገለጹት።
የክልሉ መንገድ ቢሮ ከ51 ሚሊዮን ብር በላይ ባደረገው የገንዘብ ድጋፍ በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ከ293 ኪሎ ሜትር በላይ መንገድ በመደበኛ ጥገና እየተሠራ መኾኑን በምክትል አሥተዳደር ማዕረግ የመንገድ መምሪያ ኀላፊ ጸጋው እሸቴ ገልጸዋል።

ይህም የክልሉ መንግሥት ለብሔረሰብ አሥተዳደሩ የሰጠውን ትኩረት ያሳያል ያሉት አቶ ጸጋው የመንገድ ሥራውንም በፍጥነት ለማጠናቀቅ በትኩረት እየተሠራ መኾኑንም ጠቁመዋል።

ዘጋቢ፦ ደጀን ታምሩ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የአማራ ሕዝብ ለምክክር ኮሚሽኑ ለእያንዳንዱ ጉዳይ ብቁ የኾኑ ሰዎችን መምረጥ ይጠበቅበታል” የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር
Next articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ኢትዮጵያን ከኬኒያ ያስተሳሰረውን የሱስዋ ኤሌክትሪክ ጣቢያ ጎበኙ።