“የአማራ ሕዝብ ለምክክር ኮሚሽኑ ለእያንዳንዱ ጉዳይ ብቁ የኾኑ ሰዎችን መምረጥ ይጠበቅበታል” የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር

60

ባሕር ዳር፡ የካቲት 20/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ሕዝብ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ እንዲፈቱለት የሚጠይቃቸው መሠረታዊ ጥያቄዎች አሉት። የሕገ መንግሥት ይሻሻልን፣ የወሰንና የማንነት ጥያቄ ይከበርልኝ፣ ፍትሐዊ የምጣኔ ሀብት ተጠቃሚነት ይኑር ፣ የሀሰተኛ ትርክት መሻሻል፣ በማንነት ተለይቶ መጠቃት እንዲቆምለት እና ሌሎች ጥያቄዎች አሉት። ሌሎችም ኢትዮጵያውያን በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ እንዲፈቱላቸው የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች አሏቸው።

ኢትዮጵያውያን የሚያነሷቸው ጥያቄዎች አለመመለስ ደግሞ ኢትዮጵያን በሰላም እጦት ውስጥ እንድትቆይ አድርጓታል። በማያባሩ ግጭቶች ምክንያት በርካታ ኢትዮጵያውያን ሰለባ ኾነዋል። እንደ ሀገር የገጠመውን ችግር ለመፍታት እና ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከተቋቋመ ቆይቷል።

ሀገራዊ ምክክሩ ደግሞ ኢትዮጵያውያንን በሚገባ በመወከል እና በማሳተፍ የጋራ የኾነ ውጤት ያመጣል ተብሎ ይጠበቃል። በቂ እና ብቁ ውክልና አለማድረግ እስካሁን ለነበሩ አለመግባባቶች ምክንያት ኾኖ ቆይቷል። በተለይ ደግሞ በሕገ መንግሥት ረቂቅ ላይ ውክልና ማነስ ወይም አለመኖር ዋና ችግር ኾኖ ቆይቷል። የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ በቂ ውክልና አለመኖርን እና ሌሎች ጥያቄዎችን እንደሚፈታ ይጠበቃል።

በደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር ጣዕሙ ዓለሙ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሕዝብ ዘንድ ታማኝ መኾን ይጠበቅበታል ይላሉ። ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በየጊዜው በሚያወጣቸው ሪፖርቶች ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት አንዳንድ አካባቢዎች ላይ የተሳታፊዎች ልየታ አለማድረጉን ይናገራል የሚሉት ምሁሩ የምክክር ኮሚሽን ሁልጊዜ አልጋ በአልጋ ኾኖ እንዲሠራ አይጠበቅም፣ ሁልጊዜ በተመቻቸ ሁኔታ እንዲሠራ ከተፈለገ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ መቋቋም ባላስፈለገ ነበር ይላሉ። የምክክር ኮሚሽን የተቋቀመበት ዋናው ምክንያት ሀገሪቱን ከጦርነት ለማውጣት ነው፣ ስለዚህ ጦርነት ባለባቸው አካባቢዎችም ዘልቆ ገለልተኛ በኾነ መንገድ ሥራውን እንዲሠራ ነው ኀላፊነት የተሰጠው፣ ከስጋት ነፃ የኾኑ አካባቢዎች እየፈለጉ ብቻ መሄድ ከኾነ አካሄዱ ልክ ሊኾን አይችልም፣ እንደዛ ከኾነ ውጤቱም ስኬታማ አይኾንም ባይ ናቸው።

ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ በእያንዳንዱ አካባቢ ሊደርስ ነው ኀላፊነት የተሰጠው በኀላፊነቱ ልክ መሥራት ይጠበቅበታል ነው ያሉት። ችግር ወዳለባቸው አካባቢዎች ችግር ሊገጥመው ይችላል፣ የሚገጥመውን ችግር ደግሞ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ መቋቋም አለበት ብለዋል። ችግር ባለባቸው አካባቢዎች እየገባ ገለልተኛ ተሳታፊዎችን መለየት ይችላል ነው ያሉት።
በግጭት ውስጥ ያሉ አካባቢዎች ወደ ሰላም የመመለስ የመንግሥት ተቀዳሚ ኀላፊነት መኾኑንም ገልጸዋል። የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም ሰላም ማድረግ ግድ እንደሚልም አመላክተዋል። ለብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን መሳካት የሕዝብ ሚና ከፍ ያለ መኾኑንም አንስተዋል። የምክክር ኮሚሽን ተወካዮችን ከመቀበል እና አካባቢውን ከማለማመድ ጀምሮ በርካታ አስተዋጽኦ ማድረግ ይጠበቃል ነው ያሉት።

የኔ ሀሳብ ብቻ ነው የበላይ መኾን ያለበት ብሎ ከመሟገት ራስን ማቀብ እንደሚጠበቅም ገልጸዋል። ወደ ምክክር ሲቀረብ እህታማማቾች እና ወንድማማቾች ነን ብሎ መተሳሰብ ያስፈልጋል ነው ያሉት። ለዚህች ሀገር እኩል ለፍቻለሁ እኩል ደክሜያለሁ ማለት ይገባል፣ የእኔ ድካም ብቻ ነው ከፍ ያለው የሚል ግትር አቋምም አስፈላጊ አይደለም ነው የሚሉት። ግትር መኾን አይገባም ሲባል ግን የራስን አቋም እና ማንነት ለሌላ አሳልፎ መስጠት አይደለም፣ በምክክር ሂደት ግን ሚዛናዊነት ግድ ይላል ነው ያሉት።

ኮሚሽኑ በየጊዜው የሚያወጣቸው ሪፖርቶች ከግልጸኝነት አንፃር ጥሩ ሊኾኑ ይችላሉ፣ ነገር ግን ጥርጣሬ ሊያስነሱ የሚችሉ ጉዳዮችን አለማድረግ ይመከራል ይላሉ። ሕዝብ ከጥርጣሬ በመውጣት ፣ ችግር እንኳን ቢፈጠር ሀሳብ እየሰጡ መሄድ እንጂ ለእኔ አይኾነኝም ብሎ መሸሽ አደገኛ ነው ብለዋል። ለኮሚሽኑ ግብዓት እየሰጡ፣ እየተመካከሩ መሄድ ግድ ይላል ነው ያሉት።

የምክክር ኮሚሽኑ ወደ ታች ለሚዘረጋው መዋቅር በሕዝብ ተሳትፎ የተመረጡ እና ሚዛናዊ የኾኑ ሰዎች ያስፈልጉታልም ብለዋል። ተሳታፊዎች ብቻ ሳይኾን መረጃ መዝጋቢዎች እና ሌሎችም ታምኖባቸው የሚመረጡ መኾን ይገባቸዋል ነው ያሉት።

ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት የውክልና ጉዳይ ትኩረት የሚሰጥበት መኾን አለበት ብለዋል። ውክልናን በማስፋት ጥርጣሬን ማስቀረት ባይቻል እንኳ በእጅጉ መቀነስ ይቻላል ነው ያሉት። ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት መሳተፍ የሚገባውን በሚገባ መለየት እንደሚገባም አመላክተዋል።

ኢትዮጵያ ብዝኃ ማንነት ያላት ሀገር በመኾኗ ብዙ ጥያቄዎች እና ፍላጎቶች ወደ ምክክር ኮሚሽኑ ይቀርባሉ ያሉት ምሁሩ የአማራ ሕዝብም የራሱ ጥያቄዎች አሉት ብለዋል። አሁን ላይ የአማራን ፖለቲካ እየዘወረው ያለ በማንነቴ ምክንያት ተጠቅቻለሁ የሚል ነው፤ ይሄን ሀሳብ ይዞ ከመመካከር ውጭ ሌላ አማራጭ የለም፣ በሌላ አማራጭ ሃሳቡን ቢያሳካ ዘላቂ አይኾንም ነው ያሉት። ምክክር ኮሚሽኑን እንደገለልተኛ ተቋም ወስዶ በታለመለት ዓላማ እንዲሄድ ማገዝ፣ ታላቅ እድል ነው ብሎ መቀበል እና ጉዳዮችን ከመሠረቱ እየለዩ መሄድ ያስፈልጋል ብለዋል።

የአማራ ሕዝብ በሕገመንግሥቱ አልተወከልኩም ካለ፣ ዛሬ ለምክክር ኮሚሽኑ ሙያዊ ተወካዮችን መለየት፣ ለእያንዳንዱ ጉዳይ ብቁ የኾኑ ሰዎችን መምረጥ ይጠበቅበታል ነው ያሉት። የአማራ ሕዝብ ትክክለኛ ተወካዮችን የመምረጥ ኀላፊነት እንዳለበት የተናገሩት ምሁሩ የሕዝብ ጥያቄዎችን የሚረዳ ተወካይ ያስፈልጋል ብለዋል። ሕገ መንግሥቱ ይሻሻልልኝ የሚልን ሕዝብ የሚወክል ተወካይ የሚሻሻሉትን አንቀጾች በደንብ የተረዳ እንዴትስ መሻሻል አለባቸው የሚለውን የሚያስረዳ መኾን እንደሚገባውም አንስተዋል።

የአማራ ሕዝብ የተሠራበትን የሀሰተኛ ትርክትን የሚያሻሽሉ እና እውነተኛውን ታሪክ የሚጽፉ ተወካዮች እንደሚያስፈልጉትም ተናግረዋል። ለትክክለኛው ጥያቄ ወይም አጀንዳ ትክክለኛ ሰው እንደሚያስፈልግም አመላክተዋል። ችግሮችን በምክክር መፍታት መልካም አጋጣሚ መኾኑንም ገልጸዋል። የአማራ ክልል የጋራ አጀንዳ ይዞ ለምክክር ኮሚሽን ለመቅረብ በውስጡ መግባባት እና የጋራ አጀንዳ ይዞ መውጣት ይጠበቅበታልም ብለዋል።

መሪም ኾነ ተመሪ፣ ልሂቅም ይሁን ሌላ ከአንድ ሕዝብ ነው የወጣው አንድ የጋራ አጀንዳ አለን ብሎ ማመን አለበት ነው ያሉት። የጋራ አጀንዳውን በጥርጣሬ እንዲታይ ከተደረገ ሌላ ውድቀት እንደሚያመጣም ገልጸዋል። ችግሩን ለመፍታት መንግሥት ፣ ሕዝብ እና ሙያተኞች ተቀራርበው መሥራት ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት። በመለያየት እና በመቃቃር ለውጥ እንደማይመጣም አንስተዋል። ፖለቲከኛ ከሕዝብ እንደወጣ፣ ለሕዝብ እንደሚሠራ አካል የሕዝብን ጥያቄ ማድመጥ አለበት ብለዋል። ችግሮችን ለማስታረቅ በቁርጠኝነት መሥራት ይጠበቃል ነው ያሉት።

የአማራ ሕዝብ የታወቁ አጀንዳዎች አሉት ያሉት ምሁሩ ዋናው ጉዳይ አጀንዳዎችን ይዞ ወደ ምክክር ኮሚሽን የሚሄደው ሰው ነው ብለዋል።

ተቋማትን በጥርጣሬ ማየት እና ከተቋማቱ መራቅ ችግር እንደሚፈጥርም ተናግረዋል። ታማኝ ተቋማትን መገንባት እና እድሎችን መጠቀም አዋጩ ጉዳይ መኾኑንም አመላክተዋል። ተቋማቱን አስቀድሞ መጥላት ለውጤታማነታቸው አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚያሳድርም ገልጸዋል። ተቋማቱን ከመጠራጠር ይልቅ እየደገፉ መሥራት ውጤታማ እንደሚያደርግም አመላክተዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎች በመስኖ የሚያለሙ አርሶ አደሮች ውጤታማ እየሆኑ ነው፡፡
Next articleበዋግ ኽምራ ያለውን የመንገድ ችግር ለመቅረፍ በትኩረት እየሠራ መኾኑን የብሔረሰብ አሥተዳደሩ መንገድ መምሪያ አስታወቀ።