
ባሕር ዳር፡ የካቲት 20/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ጎንደር ዞን ድርቅ በተከሰተባቸው አካባዎች ያሉ እና ለመስኖ ልማት ምቹ የኾኑ አካባቢዎች የሚገኙ አርሶ አደሮች ካለባቸው ችግር እንዲወጡ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ አርሶ አደሮች ተናግረዋል፡፡
አርሶ አደር አለቃ ግርማው እና አርሶ አደር አዳነ ቢተው ለአሚኮ እንደገለጹት በግማሽ ሄክታር መሬት ላይ ፈጥነው የሚደርሱ የአዝዕርት ዓይነቶችን በመስኖ እንዲዘሩ በመንግሥት በኩል የተደረገላቸው ድጋፍ መኖሩን ተናግረዋል፡፡
አርሶ አደሮቹ ግማሽ ሄክታር የሚኾን መሬት በቆሎ እና ጤፍ መዝራታቸውን ገልጸዋል፡፡ በአትክልት እና ፍራፍሬ እንዲያለሙ የተደረገላቸው ድጋፍ ራሳቸውን እንዲችሉ እና ከድጋፍ እንዲወጡ እንዳስቻላቸው ነው ያስረዱት፡፡
አርሶ አደሮቹ በተከሰተው ድርቅ ከገቡበት ችግር እንዲወጡ መስኖን መጠቀማቸው እንዳገዛቸው ነው የተናገሩ። ውኃገብ መሬት የሌላቸው አርሶ አደሮች ግን አሁንም ድጋፍ እንደሚሹ ነው የገለጹት፡፡
በእነሱ በኩል ግን ራሳቸውን ለመቻል እና ከእርዳታ የሚያወጣ ነገር ከመሥኖ ልማቱ ማግኘታቸውን አስረድተዋል፡፡
የሰሜን ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ ኀላፊ ጌታቸው አዳነ እንደነገሩን 41 ቀበሌ ላይ ዝናብ ያልዘነበበት እና 42 ቀበሌ ደግሞ ዝናብ በከፊል የዘነበበት መኾኑን ተናግረዋል፡፡
በዞኑ ካሉ 188 ቀበሌዎች ውስጥ በ88 ላይ ድርቅ ተከስቶ ጉዳት አድርሷል ያሉት ኀላፊው ያለውን ችግር መሰረት ተደርጎ ችግሩን ለመቀልበስ የተለያዩ ሥራዎች ሲሠሩ መቆየታቸውን አስረድተዋል፡፡
በተለይ የዕለት ምግብ መሸፈን የሚቻልባቸውን መንገዶች ለመፍጠር ጥረት ሲደረግ ቆይቷል ነው ያሉት፡፡ አርሶ አደሮቹ ከእለት ምግብ ባለፈ በቀጣይ ችግሩን መቋቋም እንዲችሉ በዞኑ በኩል የዘር አቅርቦት እንዲኖር በማድረግ ውኃ ገብ የኾኑ አካባቢዎችን እንዲያለሙ የማድረግ ተግባር መከናወኑን ገልጸዋል፡፡
በወረዳዎቹ 607 ነጥብ 3 ሄክታር መሬት እንዲለማ እና ራሳቸውን ማገዝ የሚችሉ አካባቢዎች ራሳቸውን እንዲያግዙ ለማድረግ ጥረት መደረጉን ነው ያስረዱት፡፡
በአጠቃላይ 452 ሺህ 851 ሰዎች በድርቅ መጎዳታቸውን አንስተው ከዚህ ውስጥ 7 ሺህ 696 አርሶ አደሮች ከተከሰተባቸው ጉዳት እንዲያገግሙ ለማድረግ በመስኖ ልማት እንዲሰማሩ ተደርጓል ነው ያሉት፡፡ ከተጎጅዎች አንጻር የመስኖ አቅም ያላቸው አነስተኛ ቢኾኑም እነዚህን አርሶ አደሮች ያላቸውን አቅም እንዲጠቀሙ መሠራቱን ነው ያስገነዘቡት፡፡
በአካባቢው በፍጥነት የሚደርሱ ሰብሎች ላይ ትኩረት ተደርጎ መሠራቱን የነገሩን ኀላፊው በቆሎን በስፋት ጤፍ፣ ስንዴ፣ ሽንብራ፣ አትክልት እና ፍራፍሬ ላይ ትኩረት ተደርጎ መሠራት እንዳለበት ታሳቢ ተደርጎ ስለመሠራቱ ተናግረዋል፡፡
አሁን ላይ ሰብሉ ደርሶ በመሠብሠብ ላይ ያለ እና ገና ለመሠብሰብ በሂደት ላይ ያለ ስለመኾኑም ነው ያብራሩት፡፡ በዚህም በተቻለ መጠን ጉዳቱን መቀነስ እንደተቻለም ነው የገለጹት፡፡
ኀላፊው አሁንም ቢኾን የመስኖ አቅም የሌላቸው ተጎጅዎች መኖራቸውን ተናግረው እነዚህን ተጎጅዎች ለጋሽ ድርጅቶች እና ግብረሰናይ አካላት ሊደግፏቸው እንደሚገባም ነው ያሳሰቡት፡፡
ዘጋቢ፦ ምሥጋናው ብርሃኔ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!