የተፈጠረው የሰላም እጦት በግብር ሥርዓቱ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩን የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ገቢዎች መምሪያ አስታወቀ።

22

ጎንደር: የካቲት 20/2016 ዓ.ም (አሚኮ) መምሪያው ባለፉት ስድስት ወራት ባከናወናቸው የዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ እና ቀጣይ ሥራወች ዙሪያ ከአጋሮቹ ጋር መክሯል።

በምክክሩ ተቋሙ የገቢ ግብር ቅሬታዎችን ለመፍታት የሠራው ሥራ አበረታች መኾኑ፣ ሃሰተኛ ደረሰኞችን በመለየት ፍትሐዊ የንግድ ሂደት እንዲኖር እና የሥነ ምግባር ጉድለት የታየባቸውን ሠራተኞች በማረም በኩል ባለፉት ወራት የሠራው ሥራ በበጎ ተነስቷል።

በአንጻሩ ግብር ከፋዮች በወቅቱ ግብራቸውን እንዲከፍሉ ቅስቀሳ በማድረግ በኩል ውስንነቶች መኖር፣ በነበረው የጸጥታ መደፍረስ ሳቢያ የደረሰኝ ቁጥጥሩ መላላት፣ ግብር በሚሰውሩ የንግዱ አካላት ላይ ክትትል አለመደረጉ የታዩ ውስንነቶች መኾናቸው በጥናቱ ቀርቧል።

ባለፉት ስድስት ወራት 1 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ለመሠብሠብ ታቅዶ እስካሁን 930 ሚሊዮን ብር ገደማ መሠብሠብ መቻሉን የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ገቢዎች መምሪያ ኀላፊ ሙሉቀን ብርሃኑ ገልጸዋል። ለእቅዱ አለመሳካት ደግሞ የተፈጠረው የሰላም እጦት በዋናነት ምክንያት መኾኑን አንስተዋል።

ከከተማ አሥተዳደሩ የተለያዩ ክፍለ ከተሞች የተወጣጡ የገቢ ተቋሙ አመራሮች የተፈጠረው የሰላም እጦት በሥራቸው ላይ ጫናን ፈጥሮ የቆየ ቢኾንም አቅማቸውን በመጠቀም ሥራዎችን ሲሠሩ መቆየታቸውን አንስተዋል።

የበጀት ዓመቱን የቀጣይ ቀሪ ጊዜያት በመጠቀም የታቀደውን እቅድ ለማሳካት የራሳቸውን ድርሻ እንደሚወጡ ገልጸዋል።
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ባዩህ አቡሃይ በየደረጃው የሚገኙ የገቢ ተቋሙ ሠራተኞች ፈተናወችን ተቋቁመው ተግባራቸውን ለመወጣት ያደረጉት ጥረት አበረታች መኾኑን አንስተዋል፡፡

የተሠበሠበው ገቢ ከእቅዱ በታች ቢኾንም በቀጣይ ወራት የተሻለ ገቢ ለመሠብሠብ ጥረት መደረግ እንዳለበት መልእክት አስተላልፈዋል።

የጎንደር ከተማ ነዋሪወችን ተጠቃሚ ለማድረግ የታቀዱ የልማት ተግባራትን ለማሳካት የገቢ አቅምን ማሳደግ የሚያስፈልግ በመኾኑ ሁሉም የበኩሉን መወጣት እንዳለበት ከተማ አሥተዳደሩ መልእክት አስተላልፏል።

ዘጋቢ፡- ኃይሉ ማሞ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleኢትዮጵያ በቀይ ባሕር እና በዓባይ ወንዝ ላይ ያላትን ፖሊሲ እና ስትራቴጂ የሚያሳይ ሰነድ ነገ እንደሚመረቅ የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።
Next articleድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎች በመስኖ የሚያለሙ አርሶ አደሮች ውጤታማ እየሆኑ ነው፡፡