
ባሕር ዳር: የካቲት 20/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ደኤታ ሰላማዊት ካሳ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሠጥተዋል። በመግለጫቸው የኢትዮጵያ ቀጣይ እጣ ፋንታ የተወሰነው በሁለት የውኃ አካላት ላይ መኾኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ቀጣይ እጣ ፋንታ የሚወስኑ ዓባይ እና የቀይ ባሕር መኾናቸውንም ተናግረዋል። ሁለቱ የውኃ አካላት የኢትዮጵያን ጂኦ ፖለቲካ እና ብሔራዊ ደኅንነትን በመወስን በኩል ትልቅ ሚና ያላቸው መኾናቸውን ገልጸዋል።
ሚኒስትር ዲኤታዋ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅሞች በግልጽ ስትራቴጂ መመራት ይኖርባቸዋል ብለዋል። ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር እና በዓባይ ወንዝ ላይ ያላትን ፖሊሲ እና ስትራቴጅ የሚያሳይ ሰነድ በመጽሐፍ መልኩ ተዘጋጅቶ ነገ እንደሚመረቅም ተናግረዋል። ስታራቴጂው ከሁሉም የሚለየው ዘላቂ እና ለሀገር ሕልውና ፈተና የሚኾኑ ችግሮችን ለመፍታት ታሳቢ ተደርጎ የተቀረጸ መኾኑን ነው ያስገነዘቡት።
የዓባይ ተፋሰስ እና የባሕር በር ጉዳይ አዲስ እይታ ያስፈልገዋል በሚል መያዙንም አንስተዋል። በዓባይ ውኃ አጠቃቀም፣ በቀይ ባሕር እና ተደራሽነት፣ የባሕር በር ለማግኘት የተደረገውን ጉዞ፣ በውኃ ሃብቶች ላይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ምንድን ነው የሚለውን እንደያዘም አንስተዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ደኅንነት ከሁለቱ የውኃ አካላት ጋር የተያያዘ መኾኑንም አመላክተዋል። ሁለቱን የውኃ አካላት ለመቆጣጠር የሚደረገው ትግል በዚህ ዘመን ያለ፣ በፊትም የነበረ፣ ወደፊትም የሚኖር መኾኑንም ገልጸዋል።
የውኃ አካላቱን ለመያዝ የሚደረገው ትግል በኢትዮጵያ ላይ ጫና እንደሚያሳድርም ተናግረዋል። ሰነዱ የተዘጋጀውም የተጋረጠውን ስጋት ለመቅረፍ በሚያስችል መልኩ መኾኑንም ገልጸዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!