
አዲስ አበባ: የካቲት 20/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ከሰሜን ሸዋ እና ደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር አመራሮች ጋር በ2016 ዓ.ም የግማሽ ዓመት ሥራዎች ግምገማ እና ቀጣይ ሥራዎች ላይ የሁለት ቀናት ምክክር ጀምሯል።
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ እና የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴን (ዶ.ር) ጨምሮ ሌሎች የቢሮው ኀላፊዎች፣ ከሰሜን ሸዋ እና ደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ከፍተኛ አመራሮች እና የትምህርት የሥራ ኀላፊዎች በተገኙበት የስድስት ወሩ የትምህርት ሥራ ግምገማ እና ቀጣይ ጉዞ ምክክር በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
መድረኩን የከፈቱት በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ እና የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴን (ዶ.ር) ሀገሪቱ በ2022 መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት መካከል ለመሰለፍ ለያዘችው ራዕይ ቢሮው የተማረ የሰው ኃይል ማፍራት የሚል ራዕይ ይዞ እየተሠራ እንደሚገኝ አስታውሰዋል ።
የሚፈለገውን ልማት ማስመዝገብ የሚቻለው ዘመኑን የዋጀ የተማረ የሰው ኃይል ማምረት ሲቻል ብቻ ነው ብለዋል። ጥራት ያለው ትምህርት በመስጠት ተሻጋሪ ሃሳብ ያለው ትውልድ መፍጠር አስፈላጊ እንደኾነ ዶክተር ሙሉነሽ በአጽንኦት አሳስበዋል።
አሁን ላለው ሀገራዊ እና ክልላዊ ሁኔታ ትምህርት ላይ ያለው ስብራት ውጤት ነውም ብለዋል። ከ10 ሺህ 800 በላይ ትምህርት ቤቶች በክልሉ እንዳሉ የገለጹት ኀላፊዋ በክልሉ ካለው የመንግስት ሠራተኛ 50 በመቶው የሚኾነው በትምህርት ዘርፉ ውስጥ ያሉ መኾናቸውን ጠቁመዋል።
ይህ ኃይል ለትምህርት ጥራት የድርሻውን እንዲወጣ አደራ ብለዋል። የተማሪዎች የማለፍ ምጣኔ እየወረደ መምጣት እና አዲስ ተመዝጋቢዎች ቁጥር መቀነስ ሊያሳስብ የሚገባ ነው ብለዋል።
በተዘዋዋሪ በቅኝ ግዛት ላለመውደቅ ትምህርት ላይ የህልውና ጉዳይ አድርገን በቁርጠኝነት መሥራት ይገባል ነው ያሉት። ሃብት የሚባክነው ከትምህርት ጥራት ጉድለት በሚመጣ አሠራር ነው ሲሉ በበርካታ ዘርፎች የሚስተዋሉ እንከኖችን ያነሱት ኀላፊዋ ለዚህም የትምህርት ጥራት የሁሉም ነገር ቁልፍ መኾኑን መገንዘብ አስፈላጊ ነው ብለዋል።
ስለ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ በሚነገርበት በዚህ ወቅት የትምህርት ጥራት እና አጠቃላይ ሥራዎች ያሉበትን ደረጃ ማጤን ግድ ይላልም ብለዋል ዶክተር ሙሉነሽ።መምህራን ላይ ያለባቸውን የኑሮ ጫና የሚታወቅ ቢኾንም ይህንን መለወጥ የሚቻለው ጥራት ባለው ትምህርት ብቻ መኾኑን ተናግረዋል። “ትምህርት ላይ ያለውን ስብራት ለመጠገን እና ኢትዮጵያን ለመገንባት የድርሻችንን ልንወጣ ይገባል” ነው ያሉት ዶክተር ሙሉነሽ።
ዘጋቢ፡- ድልነሳ መንግሥቴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!