
ባሕርዳር: የካቲት 20/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ፎረም የ2024 የስጋት ሪፓርት ትንበያ እንደሚያሳየው ለመጪዎቹ ሁለት ዓመታት ዓለምን ከሚያሰጓት ክስተቶች መካከል ከዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ቀጥሎ የሐሰተኛ ዜናዎች እና ሐሰተኛ መረጃዎች ስርጭት ዋናው እንደሚኾን በትንበያው አመላክቷል፡፡
የመረጃ መለዋወጫ ቴክኖሎጂዎች መዘመን እና በፍጥነት መቀያየር በዓለም አቀፍ ደረጃ የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ቁጥር በመጨመሩ ምክንያት የሐሰተኛ መረጃ ሥርጭት በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል። አሁንም በመጨመር ላይ ይገኛል። ይህ ክስተት በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ የሚዲያ አጠቃቀም ክህሎት ደረጃ አነስተኛ በኾነባቸው ሀገራት ከፍተኛ ስጋት እየኾነ መጥቷል።
ለመኾኑ የሐሰት ዜና ምንድን ነው? እንዴትስ ከሰዎች ጀሮ ይደርሳል፡፡ የሐሰት ዜና ማለት ለአንባቢያን/ ለተከታዮቻቸው የሚያሳስት ዜናን ወይም መረጃን ኾን ብሎ የማሰራጨት ተግባር ነው። ሐሰተኛ መረጃዎች የተለያየ ቅርፅ እና ዓላማ ኖሯቸው ሊሰራጩ ይችላሉ፤ ዋናው ልዩነታቸው ግን ከሥርጭቱ ጀርባ ያለው ፍላጎት ወይም ዓላማ ነው።
የሐሰት ዜና ወይም የተሳሳተ ይዘት ያለው መረጃ በንግግር፣ በጽሑፍ፣ በሕትመት፣ በኤሌክትሮኒክስ፣ በዲጂታል ሚዲያዎች ቅርጽ ይዞ በዜና እና በተግባቦት መልኩ ይቀርባል።በተጨማሪም የሐሰተኛ ዜና ዘገባዎች፣ ዘገባው በራሱ ፈጠራ፣ እውነታዎችን፣ የመረጃ ምንጮች ለማረጋገጥ የማይችሉ ይዘት ያለው ነው።
የሐሰት ዜናዎች እና መረጃዎችን ተአማኒ ከሚያስመስላቸው ምክንያቶች ጥቂቶቹ የሚከተሉት ተጠቃሾች ናቸዉ፡፡ሕዝብ ተቸገርኩበት ስለሚለው ጉዳይ ትኩረት የሚሰጥ ሲጠፋ፤ አዛኝ በመምሰል እና ስለ ጉዳዩ በማጋነን ደጋፊዎችን የሚያገኝ ሲኾን በዚህም ማስተላለፍ የፈለጉትን ሐሰተኛ መልዕክት ያስተላልፋሉ፡፡
የሐሰተኛ መረጃዎች ድግግሞሽ፣ አንድ መረጃ ተደጋግሞ የሚጻፍ ወይም የሚነገር ከኾነ የመታመን እድሉን እያሰፋ ይሄዳል፡፡ በሀገራችን ተለምዷዊ ብሂል ውሸት ሲደጋገም እውነት ይመስላል አንደሚለው፡፡ በአንፃሩ ደግሞ ብዙም ባይኾንም ጥቂት ሰዎች የሐሰት መረጃዎች ሲደጋገሙ ለማጣራት እድል ይሰጣቸዋል፡፡
የኅብረተሰቡን ክፍተት በመጠቀም ሐሰተኛ መረጃዎች ይሰራጫሉ፤ ይህ የሚኾነው እዉነተኛን መረጃ በመያዝ እና የኅብረተሰቡን ድክመት እንደ ክፍተት በመጠቀም እንዲኹም እዉነተኛዉን መረጃ በመጠምዘዝ እነሱ የፈለጉትን ሃሳብ ሊያስተላልፉ ይችላሉ ይህም መረጃው ተአማኒ ሊያስመስለው ይችላል። ምንጭ:- የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንንት አሥተዳዳር ።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!